በሊቨርፑል እና በኤቨርተን መካከል የሚደረገው የመርሲሳይድ ደርቢ ጨዋታ ተራዘመ
የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ መሪ ሊቨርፑል የአንደኛነት ደረጃውን ያጠናክርበታል የተባለው ተጠባቂ ጨዋታ የታራዘመው በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ነው

በሌላ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ በሜዳው ኖቲንግሀም ፎረስትን ይገጥማል
በመርሲሳይድ ደርቢ በሊቨርፑል እና ኤቨርተን መካከል በዛሬው ዕለት ሊደረግ የነበረው ጨዋታ መራዘሙ ተሰምቷል፡፡
ጨዋታው በእንግሊዝ ባጋጠመው “ዳራጋ” በተባለው ከፍተኛ የንፋስ ማዕበል በፈጠረው አስቸጋሪ የአየር ጸባይ ነው፡፡
የዛሬው ጨዋታ ኤቨርተን በ2025 ወደ አዲሱ ስታድየም ከመዘዋወሩ በፊት በጉዲሰንፓርክ ሁለቱ የአንድ ከተማ ክለቦች የሚያደርጉት የመጨረሻ የደርቢ ጨዋታ ነበር፡፡
የመርሲሳይድ ፖሊስ ቅዳሜ ማለዳ ላይ ጠንከር ብሎ የቀጠለውን ሀይለኛ የንፋስ መዕበል ተከትሎ ከሁለቱም ቡድኖች ሃላፊዎች ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡
ከውይይቱ በኋላ ፖሊስ ከቡድኑቹ ጋር በጋራ ባወጡት መግለጫ “ደጋፊዎችን ሊያሳዝን ቢችልም ለተጫዋቾቻችን ፣ የደጋፊዎቻችንን እና ለስታድየሙ ሰራተኞች ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ጨዋታውን ለማራዘም ተገደናል” ብለዋል፡፡
በሰአት 90 ሜትር የሚጓዘው አደገኛው የንፋስ ማዕበልን ተከትሎ በደቡባዊ ዌልስ እና በምዕራባዊ እንግሊዝ የሚገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ታዘዋል፡፡
ከአርሰናል እና ቼልሲ በ7 ነጥብ ከፍ ብሎ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ሊቨርፑል አርሰናል እና ቼልሲ በነገው ዕለት ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት የነጥብ ልዩነቱን አስፍቶ ለመቀጠል የነበረውን እድል ማጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከወራጅ ቡድን በ9 ነጥብ ከፍ ብሎ 15ተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኤቨርተን በበኩሉ ከማንችስተር ዩናይትድ 4 ለ0 ሽንፈት በኋላ የሊጉን መሪ ለመገጥም ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡
በሌሎች የሊጉ መርሐግብሮች በሳምንቱ አጋማሽ ዕሮብ በኢሜሬትስ ስታድየም ከአርሰናል ጋር ባደረገው ጨዋታ 2ለ0 ያሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ ዛሬ ምሽ 2፡30 በሜዳው ኖቲንግሀም ፎረስትን ያስተናግዳል፡፡
በአምስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ ሁለት አቻ እና አንድ ሽንፈት ያስተናገደው ዩናይትድ ደረጃውን ለማሻሻል እያደረገ የሚገኝውን ጥረት ቀጥሏል፡፡
ከምሽቱ ጨዋታ ቀደም ብለው መግለጫ የሰጡት የቡድኑ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በዛሬው ጨዋታ ተከላካይ አማካዮቹ ጆኒ ኢቫንስ እና ቪክተር ሊንደሎፍ እንደማይሰለፉ አረጋግጠዋል፡፡
ቡድኑን ከተረከቡ በሁለት ሳምንታት ውስጥ አራት ጨዋታዎችን የመሩት አሞሪም “ደጋፊዎች የቡድናቸውን ውጤታማነት በቶሎ ማየት እንደሚጓጉ አውቃለሁ፤ ቡድኑን በሂደት እየገነባነው ነው ተጨዋቾቼ ከስህተታቸው ለመታረም እና አዳዲስ ታክቲኮች ጋር ለመዋሀድ የሚያስቸገሩ አይደሉም” ብለዋል፡፡
በዚህም ከሁሉም ጨዋታዎች እየተማሩ ወደ ውጤት እንደሚቀርቡ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ማንችስተር ሲቲ ከክሪስታል ፓላስ አስቶን ቪላ ከሳውዝሀምብተን ጨዋታዎችን ያደርጋሉ::