ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሀጃጆች መካ ገብተዋል
አመታዊው የሀጅ የጸሎት ስነስርአት በመጪው አርብ በሳኡዲ አረቢያ መካ ይከናወናል
ሀጅ የእስልምና ሀይማኖት ከሚያዛቸው 5ቱ መሰረታዊ ሀይማኖታዊ ግዴታዎች መካከል አንዱ ነው
ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሀጃጆች መካ ገብተዋል።
አመታዊውን የሀጅ የጸሎት ስነስርአት ለመታደም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሀጃጆች መካ ከትመዋል፡፡ በተለያዩ የአለም ሀገራት የሚገኙ ሙስሊሞች የሚታደሙት አመታዊ ስነስርአት በሀይማኖቱ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡
እስልምና ከሚያዛቸው 5ቱ መሰረታዊ ሀይማኖታዊ ግዴታዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ይነገራል፡፡
የሳኡዲ ባለስልጣናት በመጪዎቹ ቀናት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሀጃጆች ወደ ሳኡዲ እንደሚገቡ ያስታወቁ ሲሆን በዚህኛው አመት ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሙስሊሞች ወደ መካ እንደሚመጡ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ሀጃጆች በአየር በየብስ እና በባህር ወደ ሳኡዲ በመግባት ላይ ይገኛሉ፣ በ2019 2.4 ሚሊየን ሙስሊሞች በስነስርአቱ ላይ ታድመዋል፡፡
ሳኡዲ ለሀጅ ስነስርአት የሚገቡ በመላው አለም የሚገኙ ሙስሊሞችን ለማስተናገድ ከእያንዳንዱ ሀገር ከአንድ ሽህ ሙስሊም አንድ ሰው እንዲሳተፍ ኮታ አስቀምጣለች፡፡
በዚህኛው አመት እስራኤል በሀይል ከያዘችው ዌስት ባንክ 4200 ፍልስጤማዊያን ሀጃጆች እንዲሳተፉ ሪያድ ፈቃድ ሰጥታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በመካ የሚገኙ ሀጃጆች በትላንትናው እለት በካአባ ዙርያ 7 ግዠጊዜ በመዞር ሀይማኖታዊ ስነስርአትን አከናውነዋል።
በሚሊየን የሚቆጠሩ ሀጃጆችን የምታስተናግደው ሳኡዲ ለሀይማታዊ ስነስርአቱ በርካታ ዝግጅቶችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ከ22ሺ በላይ ሀይማኖታዊ ስነስርአቱን ብቻ የሚያስተባብሩ ከተለያየ የስራ መስክ የተውጣጡ ባለሙያዎች የስራ ቅጥር በመካ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የተፈጸመ ሲሆን ከነዚህ የስራ መስኮች መካከል ኢንጂነሮች ፣ አስተዳደራዊ ሰራተኞች ፣ የጽዳት ሰራተኞች እና የህክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡
በርካታ ሰዎች ይገኙባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች የተሳታፊዎቹን ጤና ለመጠበቅ የ24 ሰአት የጽዳት ፕሮግራም ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ በተጨማሪም ደረቅ ቆሻሻዎችን የሚያጸዱ የማሽን ቴክኖሎጂንም ተግባራዊ ማድረጓ ነው የተሰማው፡፡
ከዚህ ባለፈም ከአንድሚሊየን በላይ የእርድ እንስሳትን ማስተናገድ የሚችሉ ቄራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደራጅተው ዝግጁ ሆነዋል፡፡ የመካ መዘጋጃ ቤት መሰረተ ልማቶችን ለሃጃጆች ምቹ በማድረግ ረገድ 66ሺ መንገዶችን ፣ ድልድዮችን ፣ ዋሻዎች እና የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ግንባታ አጠናቋል፡፡
የቴክኒክ እና የአገልግሎት ችግር ቢያጋጥም 24 ሰአት የሚያገለግሉ ቴክኒሻኖች በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
የደህንነት ሁኔታውን በተመለከተ በየትኛውም ሁኔታ ስጋት ሊፈጥር የሚችል ሁኔታ ቢያጋጥም በምን አይነት መንገድ እንደሚቆጣጠሩ የሳኡዲ የጸጥታ ሀይሎች በቅርቡ ወታደራዊ ትርዒት አሳይተዋል፡፡