ከአራት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ
በአማራ ክልል ተጨማሪ ተፈናቃዮች ሊኖሩ እንደሚችሉም ተገልጿል
ካሳለፍነው ነሀሴ ጀምሮ በኢትዮጵያ 12 ክልሎች ዜጎች በጸጥታ እና ድርቅ ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል
ከአራት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ፡፡
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡
እንደ ተቋሙ ሪፖርት ከሆነ ከአጠቃላይ ተፈናቀዮች ውስጥ 64 በመቶ ያህሉ በጦርነት እና ግጭት ምክንያት ሲፈናቀሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድርቅ እና ማህበራዊ ጭንቀት ምክንያት ነው፡፡
አይኦኤም ባሳለፍነው ነሀሴ እና መስከረም ወር ላይ አደረኩት ባለው ጥናት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው እየተፈናቀሉ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ትክክለኛ የተፈናቃዮችን ቁጥር ማግኘት እንዳልቻለ የገለጸው አይኦኤም ሶማሊ ክልል በድርቅ ከተፈናቀሉ ተፈናቃዮች መካከል ትልቁን ቁጥር እያስተናገደ ነውም ብሏል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን ስራ እንደሚጀምር ተገለጸ
ትግራይ ክልል ደግሞ በጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ተፈናቃዮች ያሉበት ክልል ነው የተባለ ሲሆን በአጠቃላይ ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው ከነበሩት መካከል 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለሳቸው ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ከዚህ በፊት ከመኖሪያ ቤታቸው ከተፈናቀሉ ዜጎች ውስጥ በትግራይ 59 በመቶዎቹ፣ በአማራ 15 በመቶ እንዲሁም በአፋር ደግሞ 8 በመቶ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ባሳለፍነው ሳምንት ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ በግጭት እና ድርቅ ምክንያት ለተፈናቀሉ እና ሌሎች ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርጌያለሁ ማለቱ አይዘነጋም፡፡