ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ውድቅ ካላደረገች መነጋገር እንደማትፈልግ ሶማሊያ ገለጸች
ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት እና ተመድ እንደምትወስደውም አስታውቃለች
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንዳልጣሰች መግለጿ ይታወሳል
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ውድቅ ካላደረገች መነጋገር እንደማትፈልግ ሶማሊያ ገለጸች።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሶስት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎ ሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነውም ተብሏል።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱን ተከትሎ የዲፕሎማሲ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ትገኛለች።
በዛሬው ዕለትም የኢጋድ መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ በኡጋንዳ ካምፓላ እየተካሄደ ሲሆን ከውይይት አጀንዳው መካከል የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጉዳይ ይገኝበታል።
በኢጋድ ስብሰባ ላይ እየተካፈሉ ያሉት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች በቀር ለውይይት እንደማይቀመጡ ተናግረዋል።
ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበርም ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት እና ለመንግስታቱ ድርጅት የጽጥታው ምክር ቤት እንደምትወስደውም ገልጻለች።
ኢትዮጵያ በግልጽ የሶማሊያን ሉዓላዊነት በግልጽ ጥሳለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ስምምነት ካልተሰረዘ በቀር ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችን ወትቀበልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ሌሎች ሀገራት ከሚያደርጉት የተለየ እንዳልሆነ እና የማንንም ሉዓላዊነት እንዳልጣሰች መግለጿ ይታወሳል።
ከሶማሊያ ጋርም ያላት ግንኙነት እንደከዚህ በፊቱ እንደቀጠለ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል።