በሞሮኮ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከ1000 በላይ ሰዎች ሞቱ
በሞሮኮ ማራካሽ እና አካባቢዋ በሬክተር ስኬል 6.8 ማግኒትዩድ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል
በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል
በሞሮኮ ማራካሽ ከተማ እና አካባቢዋ ላይ በሬክተር ስኬል 6.8 ማግኒትዩድ የሆነ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ መድረሱ ተገለጸ።
በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው እስካሁን 1000 ሰዎች እንደሞቱ መረጋገጡን ሮይተርስ የሀገሪቱን ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ትናንት ሌሊት 5 ሰዓት ከ30 ገደማ ላይ በደረሰው ርዕደ መሬት በርካታ ሰዎች ላይም ጉዳት ደርሷል የተባለ ሲሆን፤ አሁንም በህንጻች ፍርስራሽ ውስጥ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተነግሯል።
የሞሮኮ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አደጋውን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የሀገሪቱ ዜጎች ደም እንዲለግሱ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ እንዲረጋጉም ጠይቋል።
ርእደ መሬቱን በመፍራትም በርካታ ሞሮኳዊያን ከቤታቸው ውጪ በመውጣት መንገድ ላይ ምሽቱን ለማሳለፍ መገደዳቸውም ነው የተነገረው።
በአደጋው በርካታ ህንጻች መፈራረሳቸውም የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይም በማራካሽ እና በሌሎች ከተሞች በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ህንጻዎች ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሽሎዝ እና ሌሎች የዓልመ ሀገራት መሪዎች ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው።