ቱርክ በርዕደ መሬት ምክንያት ቤት አልባ ለሆኑ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዘጎቿ ቤት መስራት ጀመረች
ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቤቶችን ለመገንባት ቃል ገብተዋል
በርዕደ መሬቱ 520 ሽህ አፓርትመንቶችን የያዙ ከ160 ሽህ በላይ ህንጻዎች ፈርሰዋል
ቱርክ በርዕደ መሬት ምክንያት ቤት አልባ ለሆኑ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዘጎቿ ቤት መስራት ጀመረች።
በቱርክና በሶሪያ በደረሰው ርዕደ መሬት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ50 ሽህ በላይ መድረሱ ተነግሯል።
ቱርክ በዚህ ወር የደረሰውን ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ የመኖሪያ ቤቶችን መልሶ የመገንባት ስራ መጀመሯን የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
በርዕደ መሬቱ 520 ሽህ አፓርትመንቶችን የያዙ ከ160 ሽህ በላይ ህንጻዎች ፈርሰዋል ወይም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
ከፊታቸው ምርጫ የሚጠብቃቸው ፕሬዝዳንት ረሲጵ ጣይብ ኤርዶጋን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቤቶችን ለመገንባት ቃል ገብተዋል። ምንም እንኳን ባለስልጣናቱ ከፍጥነት በፊት ደህንነትን ማስቀደም እንዳለባቸው ባለሙያዎች ቢናገሩም።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ባለስልጣን ለሮይተርስ "ለበርካታ ፕሮጀክቶች ጨረታዎች እና ኮንትራቶች ተከናውነዋል። ሂደቱ በጣም በፍጥነት እየሄደ ነው" ብለዋል።
ባለስልጣኑ በደህንነት ላይ ምንም አይነት ድርድር አይኖርም በማለትም ተናግረዋል።
የቱርክ መንግስት የመጀመሪያ እቅድ 200 ሽህ አፓርትመንቶች እና 70 ሽህ ቤቶችን ቢያንስ በ15 ቢሊየን ዶላር መገንባት ነው ተብሏል።
የአሜሪካው ባንክ ጄፒ ሞርገን አንካራ ቤቶችን መልሶ ለመገንባትና ለመሰረተ ልማት 25 ቢሊዮን ዶላር እንደምታወጣ ገምቷል።
የተመድ የልማት መርሀ-ግብር (ዩኤንዲፒ) በበኩሉ በደረሰው ውድመት 500 ሽህ አዳዲስ ቤቶች ያስፈልጋሉ ብሏል።