የአረፋ በዓል በመላው ዓለም እየተከበረ ነው
በእርድ ጭምር የሚከበር በዓልም ነው አረፋ
በዓሉ የቻለ ወደ መካ በመጓዝ (ሃጅ) በማድረግ ያከብረዋል
የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉ ለ1443ኛ ጊዜ የሚከበር ነው፡፡
ኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ በጸሎትና በተለያዩ ሌሎች ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች የሚከበርም ሲሆን አቅሙ የፈቀደ ለመስዋዕትነት የሚቀርቡ እንስሳትን በማረድና ለሌላቸው በማካፈል ያከብረዋል፡፡ በዚህም የእርድ በዓል እየተባለ ይጠራል፡፡
ኢትዮጵያውያን የሃይማኖቱ ተከታዮችም እንዲሁ በመስጊዶች በመገኘትና በመስገድ ሌሎች ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶችን በማድረግ ያላቸውን ለሌላቸው ጭምር በማካፈል ያከብሩታል፡፡
የአረፋ በዓል በመጣ ጊዜ ወደ መካ ሃጅ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ ወደ ቅዱሱ ቦታ መካ በመጓዝ በአቅራቢያው ወደሚገኘው አረፋት ተራራ ተምመው የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞችም አሁን ላይ የመጨረሻ የሚባሉ የሃጅ ምዕራፎችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
በመጪዎቹ ሶስት ተከታታይ ቀናት የሚፈጸም ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓትም ይኖራል፡፡
በመላው ህዝበ ሙስሊም ዘንድ በመከበር ላይ ያለውን አረፋን በማስመልከት መሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል ሲታሰብ በመንፈሳዊውም ይሁን በሥጋዊው ዓለም ታላቅነት የሚመጣው በፈተና ውስጥ በጽናት ለማለፍ መቁረጥ ነው ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ሲሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የዐረፋ በዓል የሥነ ልቦና ጥንካሬአችን በሚፈተኑ አጋጣሚዎች መካከል ሆነን ነው የምናከብረው ብለዋል።
"በአንድ በኩል ሰላማችንን የሚረብሹና ጦራቸውን ሰብቀው ሊወጉን አድብተው የሚጠብቁ ጠላቶች በተራቀቀ ሴራ አቅማችንን ሊያዳክሙ ይተጋሉ። በሌላ በኩል የሕዳሴ ግድብ ግንባታችን ወደ ሦስተኛውና ዋናው ምዕራፍ ለማሸጋገር ከጫፍ ደርሰን ተስፋውንና ጠላቶቻችን የደቀኑብን ስጋት በቅርብ ርቀት እየተመለከትን ነው" ሲሉም ጠ/ሚ ዐቢይ ስጋቶቹን ያስቀመጡት፡፡
በመሆኑም ስጋቶቹን ባለመወላወልና በአቋም በመጽናት ፈተናና አደጋዎቹን ማለፍ ይገባልም ብለዋል፡፡
ከነብዩ ኢብራሒም መልካምነትን ተምረን የዐረፋን በዓልና ከዚያ በኋላ ያሉ ቀኖችን በመተጋገዝና መደጋገፍ እንድናሳልፍ ይጠበቃል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
አቡ ዳቢ በሚገኘውና በታላቁ ሼክ ዛይድ መስጊድ ተገኝተው በመስገድ በአሉን ማክበር የጀመሩት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለህዝበ ሙስሊሙ የእኗነን አደረሳችሁ መልዕክትን አስተላልፈዋል፡፡
ፈጣሪ በእዝነቱ ለመላው ዓለም ሰላምና መዋደድን እንዲሰጥ በመመኘትም ነው ሼክ መሃመድ እንኳን አደረሳችሁ ያሉት፡፡
ለመላው ህዝበ ሙስሊም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የሳዑዲው ንጉስ ሳልማን በኮቪድ ምክንያት ተጥለው የነበሩ እገዳዎችን በማንሳትና ጥንቃቄዎችን በማድረግ ሃጅ የሚያደርጉ ምዕመናንን ቁጥር ወደ ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡