ሰርጌ ላቭሮቭ የቡድን 20 አባል ሃገራት የውጭ ሚኒስትሮች ስብሰባን ረግጠው ወጡ
የአሜሪካ እና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያደረጓቸውን ንግግሮች አልተከታተሉምም ተብሏል
ላቭሮቭ በስብሰባው ሃገራቸው ክፉኛ መወገዟን ተከትሎ ነው
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የቡድን 20 አባል ሃገራት የውጭ ሚኒስትሮች ስብሰባን ረግጠው ወጡ፡፡
ላቭሮቭ በኢንዶኔዥያ በመካሄድ ላይ ያለውን ስብሰባ ረግጠው የወጡት በስብሰባው ሃገራቸው ክፉኛ መወገዟን ተከትሎ ነው፡፡
ሩሲያ ዩክሬንን ወራለች ያሉ የአሜሪካ እና የሌሎች ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዝግ ባደረጉት ስብሰባ ድርጊቱን ክፉኛ በማውገዝ በሩሲያ ላይ የትችት ናዳዎችን አዝንበዋል፡፡
ወረራው መቆም አለበት የሚል የትችት ድምጽ ከሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መሰማቱንም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የተናገሩት፡፡
በዚያም ምክንያት ነው ላቭሮቭ በኢንዶኔዥያ ባሊ በመካሄድ ላይ ያለውን ስብሰባ ረግጠው የወጡት፡፡
በስብሰባው የዛሬ ጠዋት መርሐ ግብር ላይ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ሩሲያን ማውገዛቸውም ተነግሯል፡፡
ላቭሮቭ ፤ ብሊንከንን ጨምሮ የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሬ ኩሌባ በበይነ መረብ ያደረጉትን ንግግር አለመካፈላቸውንም ነው ኤ.ኤፍ.ፒ የዘገበው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምዕራባውያን አጋሮቻችን በስብሰባው ስለ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ማውራታቸውን ትተው ሩሲያን ማውገዝ ላይ ተጠምደዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ብሊንከን ያገዳችሁት ስንዴ እና ሌሎችም የእህል ምርቶች እኮ የእናንተ አይደሉም ሲሉ የሩሲያ አጋር ሃገራት የዩክሬንን የግብርና ምርቶች ከማገድ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡
ሆኖም ሩሲያ በስንዴ እና በሌሎችም የእህል ምርቶች ጉዳይ ላይ ከዩክሬን እና ቱርክ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን ገልጻች።
ቱርክ ከሰሞኑ ከዩክሬን የተሰረቁ የእህል ምርቶችን የጫኑ ናቸው ያለቻቸውን የሩሲያ የጭነት መርከቦች መያዟ ይታወሳል።
የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ መገደል ስብሰባውን እንዳቀዛቀዘው ነው የተነገረው፡፡