በህንድ አንዲት ጨቅላ ስምንት እጅና እግር ኖሯት ተወለደች
የጨቅላዋ አፈጣጠር ጭንቅላትና ልብ ሳይኖረው ተጣብቆ የተወለደ ሌላ መንታ ሲኖር የሚያጋጥም ነው ተብሏል
ጨቅላዋ "ቅዱስ" ሆና ዳግም የተፈጠረች ናት በሚል በርካታ ህንዳውያን እየጎበኟት ይገኛሉ
በህንድ አንዲት ጨቅላ ስምንት እጅና እግር ኖሯት ተወለደች፡፡
ጨቅላዋ የተወለደችው በሰሜናዊ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ሃርዶይ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡
የጤና ጣቢያው አዋላጅ ባለሙያዎች ካሪና የተባለችው የጨቅላዋ ወላጅ እናት ምጥ በርትቶባት ወደ እነሱ ከመምጣቷ ውጭ እንዲህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ መሆኗን በምርመራ ጭምር አላወቀም ነበረ፡፡
ሆኖም ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ስምንት እጅና እግር ያላትን ጨቅላ በሰላም አገላግለዋል፡፡
ሶስት ኪሎ ትመዝናለች ያሏት ጨቅላ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ የተናገሩት ዶ/ር ዑመሽ ባቡ በጤና ጣቢያችን እንዲህ ዐይነት ነገር አጋጥሞን አያውቅም ነው ያሉት፡፡
በሁኔታው እና በጨቅላዋ የሰውነት ይዞታ እናትዬዋም ሆኑ ያገዟት የህክምና ባለሙያዎች ተገርመዋል፡፡ በፈጣሪ አምሳል ዳግም የተፈጠረች "ቅዱስ" ህጻን ናት ያለው የአካባቢው ማህበረሰብም ጨቅላዋን ለማየት ወደ ጤና ጣቢያው በገፍ መጉረፉ ተነግሯል፡፡
በህንድ እንዲህ ዐይነት ሁኔታዎች የተለመዱ ናቸው፡፡ በሂንዱይዝም ሃይማኖታዊ አስተምህሮት መልካም ስራ የነበራቸው ዳግም በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ "ቅዱስ" ሆነው ይፈጠራሉ (“ሪኢንካርኔሽን”) የሚል እምነት አለ፡፡
እንዲህ ዐይነቱ አፈጣጠር በምን ምክንያት ሊያጋጥም እንደሚችል የተጠየቁት ዶ/ር ዑመሽ ምናልባት ጨቅላዋ ጭንቅላትና ልብ ሳይኖረው ተጣብቆ የተወለደ ሌላ መንታ ሳይኖራት እንዳልቀረ ተናግረዋል፡፡