አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር ዩኒሴፍን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰርተዋል
የሱማሌ ክልል ምክር ቤት ክልሉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ ሙሰጠፌ መሐመድ ዑመርን የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ መረ።
አቶ ሙስጠፌ የተመረጡት በክልሉ የተካሄደውን 6ተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ባለው የአዲስ መንግስት ምስረታ መርሃ ግብር ላይ ነው። 272 መቀመጫዎች ያሉት ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ ከመረጠ በኋላ የክልሉን መሪ መርጧል፡፡
አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲመሩ መመረጣቸው ይታወሳል። የቀድሞው ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶህዴፓ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቶ ሙስጠፌን የሱማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ የመረጠው ነሃሴ 2010 ዓ.ም ላይ ነበር።
ሶማሌ ክልልን ለበርካታ ዓመታት በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የነበሩትን አብዲ ሙሐመድ ኡመርን በመተካት ነበር አቶ ሙስጠፌ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ያገለገሉት።
በ6ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ በደገሃቡር ከተማ ለክልል ምክር ቤት የተወዳደሩት አቶ ሙስጠፌ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ክልሉን ለመምራት ቃለመሃላ ፈጽመዋል፡፡
ዛሬ የሱማሌ ክልል ርዕሠ መስተዳድር ሆነው የተመረጡት አቶ ሙስጠፌ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ በመሆን መስራታቸው ይታወሳል።
በኋላም ከሀገር ወጥተው እንዲኖሩ ጫና ስለተደረገባቸው ድረስ ከነ ቤተሰቦቻቸው በኬንያ ይኖሩ ነበር። ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው መሾማቸው እስኪሰማ ድረስ አቶ ሙስጠፌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሶማሊያ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በመስራት ላይ ነበሩ።
ከሀገራቸው ከወጡ በኋላ የሕጻናት አድን ድርጅትን (ዩኒሴፍ)ን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ሰርተዋል።
አቶ ሙስጠፌ ማናቸው?
አቶ ሙስጠፋ የተወለዱት የሶማሌ ክልል መዲና ከሆነችው ከጅጅጋ ከተማ 200 ኪሎ ሜትር በምትርቀው አዋሬ የተባለች አነስተኛ ከተማ በ1964 ዓ.ም. ነው።
ትምህርታቸውን በደገሐቡር እና በሐረር የመድሐኒዓለም ትምህርት ቤቶች የተከታተሉት አቶ ሙስጠፌ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን በኢኮኖሚክስ ትምህርት አግኝተዋል።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተመሳሳይ በኢኮኖሚክስ ከለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ በተልዕኮ ትምህርት ያገኙ ሲሆን ቀደም ሲል የሶማሌ ልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም የዶክተር አብዱል መጂድ ሑሴን መምህራን ማሰልጠኛ ማዕከል ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል።