አዲሱ መንግስት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያካተተ እንደሚሆን ይጠበቃል
የምስረታ ጉባኤው የምክር ቤቱን አፈጉባኤ እና ምክትል አፈጉባኤ ሰይሟል።
በዚህም አቶ ታገሰ ጫፎ በድጋሚ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆን ተመርጠዋል።
ምክር ቤቱ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ አብላጫ ወንበር ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ የሚወክለውን ዕጩ፣ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ይሰይማል።
ብልጽግና ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ/ም የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ቦርዱ ምርጫውን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረት ብልጽግና ፓርቲ ምርጫ ከተደረገባቸው 436 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ 410ሩን አግኝቷል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሰል ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎችም መቀመጫዎችን አግኝተዋል፡፡
በወቅቱ ብልጽግና በምርጫው ካሸነፈ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ውክልና እንዲኖራቸው ያደርጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታውቀው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ብልጽግና አዲስ አበባን ጨምሮ ባሸነፈባቸው የተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች አስተዳደሮችን ሲያቋቁም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን አካቷል፡፡
ዛሬ በሚመሰረተው አዲስ መንግስት ውስጥ ለተለያዩ ሹመቶች የሚታጩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እንደሚኖሩም ይጠበቃል፡፡
በዛሬው መርሃ ግብር ለመሳተፍ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች እና እንግዶች ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ነው፡፡የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሀሙዱ ቡሀሪ የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ሚኒስትሮቻቸውን ይዘው አዲስ አበባ ገብተዋል።
የሴኔጋል ፐሬዚዳንት ማኪ ሳልንም ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፤ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም አዲስ አበባ እንደሚገቡ እየተጠበቀ ነው።