በምርጫው ብልጽግና ከፍተኛ ድምጽ ሲያገኝ 3 የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፓርላማ ወንበር አግኝተዋል
በምርጫው 4 የግል ተወዳዳሪዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማሸነፍ ችለዋል
ቦርዱ የ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ይፋ አድርጓል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ የምርጫ ውጤትን በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
ቦርዱ የተረጋገጡ የህዝብ ተወካች ምክከር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የምርጫ ውጤቶችን ነው በዛሬው ይፋ ያደረገው።
በውጤቱም መሰረት ብልጽግና ፓርቲ ምርጫ ከተደረገባቸው 436 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ 410 መቀመጫ ማገኘቱን ምርጫ ቦርዱ አስታውቋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን ምርጫ ከተደረገባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 5 መቀመጫዎች ማግኘቱንም ቦርዱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 4 የህዝብ ተወካች ምክር ቤት መቀመጫዎች እንዲሁም የጌዲዮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትም 2 የህዝብ ተወካች ምክር ቤት መቀመጫን ከደቡብ ክልል ማግኘታቸውን ቦርዱ ስታውቋል።
4 የግል ተወዳዳሪዎችም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት 1 የግል እጩ ከአዲስ አበባ 3 የግል ተወዳዳሪዎች ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ነው በምክረ ቤቱ መቀመጫ ያገኙት።
በክልል ምክር ቤትም ምርጫ ከተደረገባቸው የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ወንበር ማግኘት መቻሉን ብርዱ ይፋ ያደረገው ውጤት ያመለክታል።
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት በአፋር ክልል የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት 1 ወንበር፣ በአማራ ክልል አብን በ 6 ምርጫ ክልሎች 13 የክልል ወንበሮችን እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ጋህነን 2 መቀመጫ ማግኘት ችለዋል።
እንዲሁም በደቡብ ክልል ለክልል ምክር ቤቶች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በ4 ምርጫ ክልሎች 10 ወንበር ሲያገኝ፤ የጌዲዮ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በ2 ምርጫ ክልል 6 የክልል ምክር ቤት ወንበር ማሸነፍ ችሏል።
ቦርዱ አጠቃላይ የምርጫ ጊዜያዊ ውጤት በ10 ቀናት ውስጥ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወቃል።
ሆኖም ግን የመራጮች ድምጽ መደመር ሂደቶች አለመጠናቀቅ እና በትራንስፖርት ችግር ወደ ማዕከል ውጤት ተጠቃሎ አለመድረስ ለውጤቱ መዘግየት ምክንያቶች ሆነው ቆይቷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በውጤት ላይ የሚያነሱት አቤቱታዎች ጊዜያዊ ውጤቶች ይፋ እንዳያደርግ ምክንያት ሆኖት እንደቆየም ቦርዱ መግለጹ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ 6ኛ ዙር የተወካዮች ምክርቤትና የክልል ምክርቤት ተወካዮች ምርጫ፤ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሰኔ 14፣2013 መካሄዱ ይታወሳል።
ምርጫ በ673 የምርጫ ጣቢያዎች በአዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ተካሂዷል፤ በሶማሌ ክልል ከምርጫ ቁሳቁስ ህትመት ጋር በተያያዘ እንዲሁም በትግራይ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ምርጫ 2013 አልተካሄደም።
የሶማሌ ክልልና በተለያየ ምክንያት ምርጫ የማይሰጥባቸው ምርጫ ጣቢዎች ጳጉሜ 1 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።