አብን ምርጫ ቦርድ በኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠየቀ
ጠ/ሚ ዐቢይ በሰልፉ ላይ በተላለፈው መልእክት ላይ እርምት አለመስጠታቸው አሳዝኖኛል ብሏል አብን
አብን "በሰልፉ ላይ የጥላቻና የጥቃት ጥሪዎችን ሲመሩ የነበሩት የመንግስትና የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች ናቸው" ሲል ከሷል
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በሰልፉ ላይ “አደገኛ ንግግር” አስተላልፈዋል ባላቸው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አባላት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አብን መግለጫ ያወጣው በዛሬው እለት በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ለመደገፍ በተካሄዱ ሰልፎች ላይ አብንን የሚያወግዙ መፈክሮች መስተጋባታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የኦሮሚያ ብልግጽና ፓርቲ አባል የሆኑት የሰበታ ከተማ ከንቲባ ኦነግ ሸኔ፣አብን፣ባልደራስና ህወሃት መወገዝ አለባቸው ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኦቢኤን ዘግቧል፡፡
አብን "በሰልፉ ላይ የጥላቻና የጥቃት ጥሪዎችን ሲመሩ የነበሩት በስምና በኋላፊነት የሚታወቁ የመንግስትና የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች ናቸው" ሲል ክስ አቅርቧል፡፡
አብን የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አባላት “…ድርጅታችንን በዘር ፍጅት ወንጀል ላይ በስፋት ከተሰማሩ ሽብርተኛ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር በማጃል፣ በክልሉ በሚኖረው ሰፊ እባሳችንና ደጋፊያችንን”ለጥፋት የሚጋልጥ ንግግር አድርገዋል ብለዋል፡፡
መግለጫው አብን በምርጫ ቦርድ የተመዘገበ ህጋዊ ፓርቲ ሆኖ ሳላ አመራሮቹ “አብንን በሃሰት የሚወነጅልና የሚያወግዝ” አደገኛ መልእክት ማስተላለፋቸውን አመልክቷል፡፡
አብን በመግለጫው ምርጫ ቦርድ በአመራሮቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም “ለፈጸሙት አስነዋሪ ፍረጃ” ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
ምርጫ እየቀረበ ባለበት ስአት ሆን ተብሎ የተደረገ ንግግር ነው ያለው አብን ሰልፉን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰለፉ ላይ በተላለፉት መልእክቶች ላይ እርምት አለመስጠታቸው እንዳዘነው ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተደረገው ሰልፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
“የመንግስት ልዩ ተልዕኮ ህዝብን ማገልገል ብቻ ነው ፤ በየደረጃው ያለን የህዝብ አገልጋዮች ከእንደዚህ አይነት ድጋፍ የምንማረው እና መገንዘብ ያለብን ሀላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ የህዝብ ጥሪና አደራ እንዳለብን ሊሆን ይገባል። ዛሬ ለታየው እና ለነበረው ሰፊ ንቅናቄ መላው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪን ከልብ አመሰግናለሁ።”
አብን ያቀረበቀውን ክስ በሚመለከት የኦሮሚያ ብልጽግና ኃላፊዎችን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ግንቦት 28 ይካሄዳል ለተባለው 6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን ምልክት ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል፡፡