የሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች ወደ ዲ.አር ኮንጎ ተጉዘው በግድቡ ዙሪያ ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር መከሩ
ሼስኬዲ በሃገራቱ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እና በቀሪ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት እንዲደርሱ ለማድረግ ከኢትዮጵያ እና ግብጽ ጋር እንደሚመክሩ ገልጸዋል
ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲ ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ናቸው
የሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጉዘው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲ ጋር መከሩ፡፡
ሚኒስትሮቹ ትናንት ነበር ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ኪንሻ የገቡት፡፡
ዛሬ ከፕሬዝዳንት ሼስኬዲ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኡመር ገመረልዲን እስማኤል አስታውቀዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የተላከ የ‘እንኳን ደስ አለህ’ መልዕክትን ለፕሬዝዳንት ሼስኬዲ አድርሻለሁ ያሉት ገመረልዲን ስለ ህዳሴው ግድብ ጉዳይ ማውጋታቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በግድቡ ሙሌት እና ትግበራ የሱዳንን አቋም አንጸባርቄያለሁ ያሉም ሲሆን ሙሌቱ ‘አስገዳጅ’ ስምምነት ላይ ከመደረሱ በፊት መጀመር እንዳልነበረበት አስታውቀዋል፡፡
ገመረልዲን የአፍሪካ ህብረት ሶስቱን ሃገራት በማቀራረብ ረገድ ስለተሰጠው ሚና አውግተናልም ብለዋል፡፡
የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ (ፕ/ር)ም በገመረልዲን በተመራው ልዑክ ውስጥ ነበሩ፡፡ በልዑኩ የሚኒስቴሩ ባለሙያዎች የተካተቱም ሲሆን በኪንሻሳ የሱዳን አምባሳደር ተገኝተዋል እንደ ሃገሪቱ ዜና አገልግሎት ዘገባ፡፡
ፕሬዝዳንት ሼስኬዲ ቀጣዩ የህብረቱ ሊቀመንበር ናቸው፡፡
ሱዳንም ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ትፈልጋለች፡፡ ከአሁን ቀደም በህብረቱ በኩል ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች እንዲጓተቱ እና የደቡብ አፍሪካ የሊቀመንበርነት ጊዜ ሳይጠናቀቅ መቋጫ እንዳያገኙ ለማድረግ ስትሰራ ነበረች፡፡ ይህንንም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀደም ባሉ መግለጫዎቹ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም በሃገራቱ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡ በቀሪ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት እንዲደርሱ ለማድረግ ከኢትዮጵያ እና ግብጽ ጋር እንደሚመክሩም ነው አስረግጠው የተናገሩት፡፡
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴም ትናንት ወደ ኪንሻሳ ተጉዘው በግድቡ እና ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ቀደም ሲል በበጀት እጥረት ምክንያት ተዘግቶ የነበረውን በኪንሻሳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መልሶ ለመክፈት መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
ሁለቱ ሃገራት በአቪዬሽን ዘርፍ ስምምነት ያላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወደ ኪንሻሳ፣ሉቡምባሺ እና ጎማ ከተሞች ይበራል፡፡
ሼስኬዲ በመጪው ሳምንት የህብረቱን ሊቀ መንበርነት ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ እንደሚረከቡ ይታወቃል፡፡