ቻይና ከ8 ዓመታት በኋላ የዓለምን ኢኮኖሚ ትመራለች ተባለ
ቀድሞ ከነበረው ትንበያ በ5 ዓመት ባጠረ ጊዜ ውስጥ ነው በኢኮኖሚው ቀዳሚ ትሆናለች የተባለው
የኮሮናን ተጽዕኖ በፍጥነት መቆጣጠሯ የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤትነትን ከአሜሪካ እንድትረከብ ያስችላታል ተብሏል
ቻይና በ 2028 የዓለም ትልቁን ኢኮኖሚ በመገንባት የአሜሪካን ደረጃ እደምትረከብ የኢኮኖሚ እና የንግድ ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡
ቻይና ከአሜሪካ የኢኮኖሚ ደረጃን እንደምትረከብ ከዚህ በፊት የተገመተ ቢሆንም ቀደም ሲል ከተጠበቀው ከአምስት ዓመት ቀደም ብላ መሪነቱን እንደምትረከብ ነው የተገመተው፡፡
የዚህ ትንበያ ምክንያትም ቤጂንግ አጋጥሟት ከነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፍጥነት ማገገም መቻሏ ነው ተብሏል፡፡
መሰረቱን በብሪታንያ ለንደን ያደረገው የኢኮኖሚ እና የንግድ ምርምር ማዕከል ፣ የቻይና ዓመታዊ ዕድገት ከ2021 እስከ 2025 ድረስ 5 ነጥብ 7 በመቶ እንደሚሆንም ግምቱን አስቀምጧል፡፡ በዋሺንግተንና ቤጂንግ መካከል የኢኮኖሚ ሽኩቻ ቢኖርም የኮሮና ቫይረስን በመከላከልና በመቆጣጠር ግን ቻይና ባለድል ናት ብሏል የኢኮኖሚ እና የንግድ ምርምር ማዕከል፡፡ በመሆኑም ሁለቱ ሀገራት ኮሮናን በመከላከል ረገድ ያሉበትን ልዩነት ግምት ውስጥ በማስገባት ፣ ማዕከሉ ቀድሞ ከነበረው ትንበያ 5 ዓመታትን ቀንሶ ከዛሬ 8 ዓመታት በኋላ የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ቻይና ትሆናለች ብሎ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ የኮሮና ቫይረስን መከሰት ሪፖርት ያደረገችው የመጀመሪያዋ ሀገር ቻይና ብትሆንም በሀገሪቱ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ የጣለቻቸው የእንቅስቃሴ ገደቦች በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመግታት እና ኢኮኖሚውንም ከውድቀት ለመታደግ አስችሏል ነው የተባለው፡፡
ቻይና ከ2021 እስከ 2025 እ.አ.አ 5 ነጥብ 7 በመቶ እንደምታድግ የሚጠበቅ ሲሆን ከ 2026 እስከ 2030 ደግሞ 4 ነጥብ 5 የኢኮኖሚ ዕድገት ይኖራታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የዓለምን ኢኮኖሚ በሶስተኛ ደረጃ የምትመራው ጃፓን ባለችበት ትቀጥላለች ተብሎ ተገምቷል፡፡