የአፍሪካ ህብረት መዋቅር 50 በመቶ በሴቶች ሊደራጅ ይገባል -ፕሬዘዳንት ራማፎዛ
የአፍሪካ ህብረት መዋቅር 50 በመቶ በሴቶች ሊደራጅ ይገባል -ፕሬዘዳንት ራማፎዛ
አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ሲርል ራማፎዛ አንድ ሁለተኛው የህብረቱ መዋቅር በሴቶች እንዲመራ እሰራለሁ በማለት ለ33ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ቃል ገብተዋል፡፡
ፕሬዘዳንት ሲርል ራማፎዛ የግብፁን ፕሬዘዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲን በመተካት ነው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት፡፡
ከምርጫው በኋላ በሴቶች ጉዳይ ላይ ረዘም ያለ ንግግር ያደረጉት ፕሬዘዳንቱ ያለሴቶች እኩል ተሳትፎ ምንም ለውጥ ማምጣት እንደማይቻልም ገልጸዋል።
በሊቢያ፣ በደቡብ ሱዳንና በሌሎችም ግጭት ባለባቸው ሀገራት እልባት ለማምጣት ከተቋቋሙ ኮሚቴዎች እና ከሌሎችም አጋሮች ጋር በትብብር በመስራት የጥይት ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን በፍጥነት እውን ለማድረግ ዛሬውኑ ስራችንን በቁርጠኝነት መጀመር አለብንም ብለዋል።
አህጉራዊው ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ተግባራዊነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይም በፓሪሱ ስምምነት መሰረት ሌላው በቀጣይነት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት ጉዳይ እንደሚሆን ተናግረዋል።
እንደሁሉም ንግግር አድራጊዎች ሁሉ ስለፍልስጤም ያነሱት ራማፎዛ አግላዩ የአሜሪካ የሰላም እቅድ ደቡብ አፍሪካ ያሳለፋቸውን የ “አፓርታይድ” ዘመን ያስታውሰናል ብለዋል። ሁሉም አካላት ያልተሳተፉበት እቅድ ፈጽሞ ተቀባይነት አይኖረውም ሲሉም ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንቱ የንግግር መክፈቻ ስለ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነት ማውራት ነበር። ኢትዮጵያ ዘመናዊ እርሻን ከመጀመር ጀምሮ የራሷን ፊደል የቀረጸች፣ የትናንት ስልጣኔዋን የሚመሰክሩ በርካታ ቅርሶች ያሏት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሰረተች እና አሁንም ከፍተኛ ሀላፊነት በመወጣት ላይ ያለች መሆኗን በማውሳት የአህጉሪቱ ባለውለታ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ንግግር አድራጊዎች የኖቤል የሰላም ሽልማትን በማሸነፋቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የእንኳን ደስ አለዎት" መልእክት አስተላልፈዋል።