ፖለቲካ
ሩስያ ባደረሰችው አዲስ ድብደባ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ጨለማ ላይ ናቸው ተባለ
የዩክሬን ጦር ሩሲያ ከላከቻቸው 15 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ውስጥ 10ሩን መትቼ ጥያለሁ ብሏል
ሞስኮ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ አነጣጥራለች ተብሏል
ሩስያ ባደረሰችው አዲስ ድብደባ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ጨለማ ላይ ናቸው ተባለ።
በዩክሬን ኦዴሳ ወደብ ላይ የሚገኙ “ወሳኝ ያልሆኑ” መሰረተ ልማቶች ኃይል አጥተዋል ተብሏል።
ሩሲያ በኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ሁለት የኃይል ተቋማትን እንደመታችና 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ኃይል ማጣቱን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
"በኦዴሳ ክልል ያለው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው" ሲሉ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ በምሽት የቪዲዮ ንግግራቸው አሳውቀዋል።
"እንደ አለመታደል ሆኖ ጥቃቶቹ ወሳኝ ናቸው። ስለዚህ ኤሌክትሪክን ወደ ነበረበት ለመመለስ ሰዓታት ብቻ ሳይሆን ጥቂት ቀናትን ይፈጃል" ብለዋል።
ከጥቅምት ወር ጀምሮ ሞስኮ የዩክሬንን የኃይል መሠረተ ልማት በከፍተኛ ሚሳይል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች በመደብደብ እንዳነጣጠረች ሮይተርስ ዘግቧል።
ኖርዌይ የዩክሬንን የኃይል ስርዓት ለመመለስ 100 ሚሊዮን ዶላር እየላከች መሆኑን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ተናግረዋል።
የኦዴሳ ክልላዊ አስተዳደር ቃል አቀባይ ሰርሂ ብራቹክ እንደተናገሩት ለከተማዋ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል "በሚቀጥሉት ቀናት" ወደ ነበረበት ይመለሳል። ነገር ግን አውታሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት መመለስ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ሊወስድ ይችላል ተብሏል።
የዩክሬን ጦር በማህበራዊ የትስስር ገጹ እንዳስታወቀው 15 ሰው አልባ አውሮፕላኖች በደቡባዊ ኦዴሳ እና ሚኮላይቭ ክልሎች ኢላማዎችን ሞክረው 10ቹ በጥይት ተመተዋል።
ቴህራን ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን ለሞስኮ አላቀረብኩም በማለት አስተባብላለች። ኪየቭ እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ደግሞ ኢራንን ውሸታም እያሉ ነው።
ኪየቭ ሩሲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢራን ሰራሽ የሆኑ “ሻሄድ-136” ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በዩክሬን ኢላማዎች ላይ አስወንጭፋለች ያለ ሲሆን፤ ጥቃቶቹ በንጹሀን ህይወት ላይ እያደረሰ ባለው አስከፊ ተጽእኖ የጦር ወንጀል ነው ብላለች።
ሞስኮ በበኩሏ ጥቃቱ እርምጃውን ሕጋዊ ነው በማለት በሰላማዊ ሰዎች ላይ አላነጣጠረንም በማለት ምላሽ ሰጥታለች።