ሞስኮ በዩክሬን የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ተከታታይ ማፈግፈግ እያደረገች ነው ተብሏል
ፑቲን የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተናገሩ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሰራዊታቸው በዩክሬን ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሊዋጋ እንደሚችል ገልጸዋል።ይሁን እንጂ ለሁለተኛ ጊዜ የወታደር ጥሪ እንደማይደረግ ተናግረዋል።
ፑቲን ከዘጠኝ ወራት በፊት ስለጀመረው ጦርነት ቆይታ እምብዛም እንደማይናገሩ የጠቀሰው ሮይተርስ፤ በቴሌቪዥን በተላለፈ ስብሰባ ላይ "ለታማኞች" ጦርነቱ ለተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ይችላል ብለዋል።
"ይህ ረጅም ሂደት ሊሆን ይችላል" ሲሉ ጦርነቱን ገልጸዋል።ሩሲያ ከሀምሌ ወር ጀምሮ በምስራቅ እና በደቡብ ከሚገኙ የዩክሬን ግዛቶች ማፈግፈጓ የተነገረ ሲሆን፤ ለዚህም የኬቭ የጦር መሳሪያዎች ክምችት በምዕራባዊያን ልገሳ ዳጎስ ማለቱ ነው ተብሏል።
ሞስኮ በዩክሬን የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ተከታታይና ጉልህ የሆነ ማፈግፈግ ውስጥ እንድትገባ ተገድዳለች ተብሏል።
ዩክሬን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ጥልቅ ግንኙነት የጸጥታ ስጋት መሆኑን በመግለጽ ሩሲያ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻዋን" ባለፈው የካቲት ወር መጀመሯ አይዘነጋም።
ዩክሬን እና አጋሮቿ "ወረራ" ባሉት ጦርነት የሞስኮን እርምጃ "መሬት ነጠቃ ነው" ይላሉ። ፑቲን በንግግራቸው የኒውክሌር ጦርነት ስጋት እየጨመረ ነው ያሉ ሲሆን፤ ነገር ግን ሩሲያ በግዴለሽነት እንደዚህ አይነት የጦር መሳሪያ እጠቀማለሁ ብላ አትዝትም ብለዋል።
ፑቲን "አላበድንም፤ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ምን እንደሆኑ እንገነዘባለን" ሲሉ ከምዕራባዊያን ለሚቃጣባቸው ውንጀላ ምላሽ ተሰጥተዋል።
"እነዚህ አቅሞች ከየትኛውም የኒውክሌር ሀገር በበለጠ በላቁ እና በዘመናዊ መልኩ አሉን። ነገር ግን ይህንን መሳሪያ እየነቀነቅን በዓለም ዙሪያ ልንሮጥ አንችልም" ብለዋል።