በሌላ በኩል ሩስያና ኢራን በዩክሬን ጦርነት የጀመሩት ትብብር እንዳሳሰበው ዋይት ሀውስ ገልጿል
አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፎችን ማድረጓን አስታወቀች።
ዋሽንግተን የኬቭን የአየር መከላከያ ስርአት የሚያግዙና የድሮን ጥቃቶችን የሚያከሽፉ 275 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ መሳሪያዎችን ነው የላከችው።
የዋይትሀውስ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ የሩስያ እና ኢራን ዘርፈብዙ ወታደራዊ ትብብር አሳስቦናል ብለዋል።
ይህን የሞስኮ እና ቴህራን ትብብር ለመስበርም የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን ማልለታቸውንም ሬውተርስ ነው ያስነበበው።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የብሪታንያ አምባሳደር ባርባራ ውድዋርድ፥ ኢራን ለዩክሬኑ ጦርነት የሚውሉ በመቶዎች የሚቆጥሩ ድሮኖችን ለሩስያ መላኳን ገልጸዋል።
ለዚህ ውለታዋም ከሞስኮ ተዋጊ አውሮፕላኖች እንደሚቀርቡላትና የሀገራቱ ወታደራዊ ትብብር ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ መምጣቱን ነው አምባሳደሯ የተናገሩት።
ስማቸው ያልተጠቀሱ የኢራን ዲፕሎማቶችም ቴህራን ተጨማሪ ድሮኖችን እና የምድር ለምድር ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ለሞስኮ ለማቅረብ መስማማቷን መናገራቸው በሬውተርስ ዘገባ ተጠቅሷል።
ይሁን እንጂ ሁለቱ ሀገራት ከምዕራባውያኑ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ከሰሞኑ ባስተለለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ የዩክሬኑ ጦርነት አንድ ቀን በድርድር እንደሚያልቅ፥ ነገር ግን በምዕራባውያኑ ላይ ያላቸው እምነት መሟጠጡን ተናግረዋል።
ምዕራባውያን ሞስኮን ለማጥቃት ኬቭን እየተጠቀሙባት መሆኑንና የልዕለ ሃያልነት ፉክክራቸው የአለምን ሰላም አደጋ ላይ መጣሉንም ነው ያነሱት።
ፕሬዚዳንቱ በተለይም ፈረንሳይ እና ጀርመን በ2014 እና 2015 የተደረሱ ስምምነቶችን ጥሰው ለኬቭ መሳሪያ ማቀበላቸውን ተቃውመዋል።
አሜሪካ ግን የሩስያን የቀጠናው ተስፋፊነት ለመግታት ለዩክሬን የጦር መሳሪያም ሆነ የሰብአዊ ድጋፍ ማድረጌን እቀጥላለሁ ብላለች።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሊዩድ ኦስቲን፥ ሩስያ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ክምችቷን እያሳደገች መሆኑ አሜሪካን ያሰጋታል ነው ያሉት።
ፕሬዚዳንት ፑቲን “ሩስያን በኒዩክሌር ለማጥቃት የሚያስብ ሀገር ካለ ከምድረ ገጽ እናጠፋዋለን” የሚል ንግግር ማድረጋቸውንም ሃላፊነት የጎደለው ነው ብለውታል ሚኒስትሩ።
የሁለቱን ሀገራት የእጅ አዙር እና የቃላት ጦርነት ለማለዘብ ትናንት ዲፕሎማቶቻቸው በኢስታንቡል መክረዋል።
ይሁን እንጂ የዩክሬን ጦርነት ጉዳይ የውይይቱ አካል አይደለም ነው የተባለው።
የካቲት 24 2022 የተጀመረው የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት አሁንም መቋጫ አላገኘም።