ትዊተር የፕሬዚዳንት ቡሃሪን ፅሁፍ ማጥፋቱን ተከትሎ በናይጄሪያ ለ7 ወራት እገዳ ላይ ነበር
ለሰባት ወራት ትዊተር በሀገሯ እንዳይሰራ አድርጋ የነበረችው ናይጄሪያ 26 ቢሊየን ዶላር መክሰሯን ተቋማት አስታወቁ፡፡
ቢዝነስ ዴይሊ እንደዘገበው ከሆነ ናይጄሪያ ትዊተርን ዘግታ በመቆየቷ ከፍተኛ ኪሳራ ተከስቷል። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትዊተር እገዳ ምክንያት ሰራቸውን በአግባቡ መስራት ባለመቻላቸው ካሳ መጠየቃቸው ተሰምቷል።
የትዊተር ኩባንያ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ የጻፉትን በማጥፋቱ ምክንያት መተግበሪያው በሀገሪቱ እንዳይሰራ ታግዶ ነበር።
ትዊተር የፕሬዝዳንቱን ጹሑፍ ያጠፋው ሕጉን እንደሚጥስ በመጥቀስ መሆኑን ተከትሎ ነበር። የናይጄሪያ መንግስት ቃል አቀባይ ፕሬዝዳንቱ ሃሳባቸውን የመግለጽ መብት እንዳላቸው ገልጾ ትዊተር ትክክል ያልሆነ ስራ ነው የሰራው ብሎ ነበር።
የሌጎስ የንግድና ኢንዱስትሪ ማህበራት እንዳስታወቀው በሰባት ወራት ውስጥ ትዊተር ስራ ላይ ባለመቆየቱ በሀገሪቱ ላይ የ26 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ወይም የ 10 ነጥብ 72 ትሪሊዮን የናጄሪያ ናይራ ኪሳራ መድረሱን ገልጿል።
ኪሳራው የተከሰተው
ትዊተር በመታገዱ ምክንያት የኢንተርኔት ግብይት በመቆሙ ኪሳራው መከሰቱን የናጄሪያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያድግ የሚደርግ በመሆኑ መንግስት ምቹ መንገድ መፍጠር አለበት ተብሏል።
ትዊተር በመታገዱ ምክንያት ናይጄሪያ በሰዓት 251 ሺህ ዶላር እንደምታጣ በዓለም ላይ ኢንተርኔት ሲጠፋ ምን ያህል ኪሳራ እንደሚከሰት የሚያጠናው ኔት ብሎክ ገልጿል።
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ የትዊተር ዕገዳ ከተነሳ በኋላ መተግበሪው ላይ ምንም ጹሑፍ አለመጻፋቸው ተሰምቷል።