ናይጄሪያዊቷ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመምራት ብቸኛዋ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ቀረቡ
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዋ ናይጄሪያዊት ሃገራቸውን ለሁለት ጊዜያት በፋይናንስ ሚኒስትርነት አገልግለዋል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ኦኮንጆ ዓለም አቀፉን ድርጅት እንዳይመሩ አግዶ ነበር
የቀድሞዋ የናይጄሪያ የፋይናንስ ሚኒስትር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዊአላ የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመምራት ከቀረቡ እጩዎች መካከል ብቸኛዋ ተወዳዳሪ ሆነዋል ተባለ፡፡
ኦኮንጆ የደቡብ ኮሪያ የንግድ ሚኒስትር ራሳቸውን ከእጩነት ማግለላቸውን ተከትሎ ነው ብቸኛዋ እጩ የሆኑት፡፡
ዮ ሚዩንግ ሂ ራሳቸውን ያገለሉት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ድጋፍ ባለማግኘታቸው ነው፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኦኮንጆ ዓለም አቀፉን ድርጅት እንዳይመሩ አግዶ ነበር፡፡
ይህም የተቋሙን አዲስ መሪ ለመምረጥ የተጀመረውን ሂደት አስተጓጉሎ ቆይቷል፡፡
በድርጅቱ አሰራር መሠረት መሪ የሚመረጠው በአባል ሃገራቱ ስምምነት ነው፡፡ ከአባላቱ መካከል አንዱ ካልተስማማ ሃሳቡ ውድቅ ይሆናል፡፡
ኦኮንጆ ሰፊ ድጋፍ ቢኖራቸውም በአባል ሃገራቱ መካከል ስምምነት ባለመኖሩ ፣ በተለይ አሜሪካ ባለመስማማቷ ምክንያት ነው ሳይመረጡ የቆዩት፡፡ በዚህም አዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት (2021) ከመግባቱ በፊት መመረጥ የነበረበት የድርጅቱ አዲስ መሪ ሳይመረጥ እስካሁን ቆይቷል፡፡ ይህን የተቃወሙ የአሜሪካ ባለስልጣናት አዲሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የኦኮንጆን እጩነት እንዲደግፉ በመጠየቃቸው አሜሪካ የናይጄሪያዊቷን መመረጥ ደግፋለች፡፡
በዚህም የ67 ዓመቷ አፍሪካዊት ብቸኛዋ ዓለም አቀፉን ድርጅት ለመምራት የቀረቡ እጩ ሆነዋል፡፡
የሚሳካላቸው ከሆነ ድርጅቱን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት ይሆናሉ፡፡
ድርጅቱ አዲስ መሪ መምረጥ ያስፈለገው ብራዚላዊው ሮቤርቶ አዝቬዶ የስልጣን ዘመናቸው ከመጠናቀቁ ከአንድ ዓመት በፊት ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ በመወሰናቸው ነው፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዊአላ (ዶ/ር) ሃገራቸውን ለሁለት ጊዜያት በፋይናንስ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
እስካሁን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ያልቻለችው ኢትዮጵያ ፣ የአባልነት መታወቂያ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ቀጥላለች፡፡