ከ80 በመቶ በላይ አሜሪካዊያን ሀገራቸው በተሳሳተ መንገድ ላይ እንዳለች ያምናሉ ተባለ
እድሜያቸው 55 እና ከዛ በላይ የሆኑ አሜሪካዊያን ሀገራቸው በትክክለኛው መንገድ ላይ ናት ብለው ያምናሉ ተብሏል
የአሜሪካው ሞንማውዝ የተሰኘው ዩንቨርስቲ በአሜሪካ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል
ከ80 በመቶ በላይ አሜሪካዊያን ሀገራቸው በተሳሳተ መንገድ ላይ እንዳለች እንደሚያምኑ ጥናት አመለከተ።
የአሜሪካው ሞንማውዝ ዩንቨርስቲ ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ አሜሪካዊያን አሁን ባለው አስተዳድር ላይ ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ ጥናት አካሂዷል
በዚህ ጥናት ላይ 978 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በጥናቱ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል ከ80 በላይ ያህሉ አሜሪካ በተሳሳተ መንገድ እየተጓዘች እንደሆነ ያምናሉ።
በጥናቱ ከተሳተፉት ውስጥ እድሜያቸው 55 እና ከዛ በላይ ከሆናቸው ሰዎች ውስጥ 16 በመቶዎቹ ግን ሀገራቸው በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆኗን ያምናሉ ሲል ዘ ሂል የተሰኘው የአሜሪካው ሚዲያ ዘግቧል።
በዚህ ጥናት መሰረት አሜሪካ በታሪኳ በህዝቧ ዝቅተኛ ግምት የተሰጠው የጥናት ውጤት አሳይታለች ተብሏል።
ዩንቨርሲቲው ግንቦት ወር ላይ ተመሳሳይ ጥናት ማካሄዱ የተገለጸ ሲሆን በሀምሌ ወር ላይ የተገኘው የጥናት ውጤት ግን ሀገራቸው በተሳሳተ ጎዳና ላይ እንደሆነች የሚያምኑ አሜሪካዊያን ቁጥር በ9 በመቶ ጨምረዋል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ከመላው የአሜሪካ ግዛቶች የተካተቱ ሲሆን በዚህ ጥናት መሰረት አሜሪካ በታሪኳ ከፍተኛው ችግር ላይ ትገኛለች ተብሏል።
በትናቱ ከተሳተፉ ሰዎች ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች አሜሪካ በተሳሳተ መንገድ ላይ ነች ብለው ያምናሉም ተብሏል።
በጥናቱ ከተሳተፉ የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ውስጥ 6 በመቶዎቹ ብቻ ሀገራቸው በትክክለኛውም መንገድ ላይ ናት የሚል አመለካከት እንዳላቸው ተገልጿል።
በአሜሪካ የጋዝ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ፣ እና የኑሮ ውድነቱ የአሜሪካዊያን ዋነኛ የወቅቱ ችግር እንደሆነም በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች ተናግረዋል።
ይሄንንም ተከትሎ በጥናቱ ከተሳተፉ አሜሪካዊያን ውስጥ 38 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካዊያን በቅርቡ የሚካሄደውን የኮንግረስ ምርጫ ዲሞክራቶች እንዲቆጣጠሩት ሲፈልጉ 36 በመቶዎቹ መላሾች ደግሞ ኮንግረሱን ሪፐብሊካኖች እንዲይዙት እንደሚፈልጉም ጥናቱ ያሳያል።