አብዛኞቹ ዴሞክራቶች በ2024 ምርጫ ከጆ ባይደን ይልቅ ሌላ ሰው እንዲወዳደር ይፈልጋሉ ተባለ
ከዴሞክራቶች ውስጥ 26 በመቶ ብቻ ባይደን በድጋሚ በእጩነት እንዲቀርቡ ይፈልጋሉ
የቀድሞ ፐሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2024 ምርጫ በድጋሚ ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል
ከአሜሪካው ዴሞክራት ፓርቲ አባላት ውስጥ አብዛኞቹ ጆ ባይደን በ2024 ፐሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ በሌላ ሰው እንዲተኩ ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለፀ።
በዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ላይ በተደረገ ድምጽ የማሰባሰብ ሂደት 26 በመቶ ብቻ ጆ ባይደን በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በእጩነት እንዲቀርቡ ፍላጎት አለሳይተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተወዳጅነት እና ተቀባይነት በ2020 ድጋፍ በሰጧቸው ደጋዎቻቸው ዘንድ ጭምር እያሽቆለቆለ መምጣቱም ተነግሯል።
የኒው ዮርክ ታይምስ ሲዬና ኮሌጅ በትናትናው እለት ሲያሰባስበው የነበረውን ድምጽ ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አጠቃላይ ተቀባይነት ደረጃ በ33 በመቶ መሆኑ ተመላክቷል።
የአስተያየት ማሰባሰብ ስራው የተሰራው በአሜሪካ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን በርካታ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮች ባይደን በ2024 ምርጫ በድጋሚ እንዲወዳደሩ ፍላጎት እንደሌላቸው መዘገባቸውን ተከትሎ ነው።
የኑሮ ውድነት፣ የኣለም አቀፍ ቀውስ፣ በቅርቡ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ለሴቶች የተሰጠውን ህገ መንግስታዊ የውርጃ መብት መግፈፍ ለፕሬዝዳንት ባይደን ተቀባይነት መቀነስ በምክንያትነት ተቀምጠዋል።
በዚህም 64 በመቶ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ለ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከባይደን ይልቅ ሌላ እጩ መቅረብ እንዳለበት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 33 በመቶው የፕሬዝዳንቱን እድሜ በምንያትነት ያስቀመጡ ሲሆን፤ 32 በመቶው ደገሞ የፕሬዝዳንቱን የስራ አፈጻጸም ደካማነትን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ “ጆ-ባይደን አሜሪካን እያዋረዳት ስለሆነ በ2024 ድጋሚ ለምርጫ ልወዳደር እችላለሁ” በማለት ፍንጭ መስጠታቸው አይዘነጋም።
እንደፈርነጆቹ በ2020 በአሜሪካ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ጆ-ባይደን ድል ቢቀዳጁም አወዛጋቢው ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለታቸው ደጋፊዎቻቸው በርካታ ድርጊቶች ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወሳል።