ፊሊፒንስ 40 ሺህ ቻይናዊያንን ከሀገሯ እንደምታባርር ገለጸች
ፊሊፒንስ ከቻይና አቋማሪ ድርጅቶች በየዓመቱ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እያገኘች ነው
ፊሊፒንስ 175 በቻይናዊያን የተያዙ የቁማር ድርጅቶችን እንደምትዘጋም አስታውቃለች
ፊሊፒንስ 40 ሺህ ቻይናዊያንን ከሀገሯ እንደምታባርር ገለጸች።
የፊሊፒንስ ፍትህ ሚኒስቴር እንደገለጸው በቁማር ድርጅት ዘርፍ የተሰማሩ 40 ሺህ ቻይናዊያንን ከሀገሩ እንደሚያባርር ገልጿል።
ቻይናዊያን በተለይም ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ በበይነ መረብ የታገዘ የቁማር ድርጅቶች እየተስፋፉ መጥተዋል።
ቻይናዊያን በሀገራቸው በበይነ መረብ የታገዘ የቁማር ድርጅት መክፈት አለመቻሉን ተከትሎ ነበር ወደ ፊሊፒንስ የመጡት።
ከፊሊፒንስ ሆነውም በቻይና ለሚኖሩ ዜጎች የቁማር አገልግሎቱን በማቅረብ ገቢ በማግኘት ላይ ቆይተዋል።
እነዚህ የቻይናዊያን የቁማር ድርጅቶች ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የፊሊፒንስ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋልም ተብሏል።
ይሁንና የኮሮና ቫይረስ እና የፊሊፒንስ መንግስት በአቋማሪ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ግብር መጣሉን ተከትሎ ቻይናዊያን ከስራ ውጪ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል።
የስራ አጥ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎም ቻይናዊያን እራሳቸው የራሳቸው ሀገር ዜጎችን ማገት፣ ግድያ እና ሌሎች ወንጀሎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
በዚህም መሰረት ፊሊፒንስ ለቻይናዊያን የንግድ ሰዎች ሰትታው የነበሩ የስራ ፈቃዶችን ለመንጠቅ መወሰኗን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የፊሊፒንስ መንግስት ከቻይናዊያን አቋማሪ ድርጅቶች በዓመት ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እያገኘ እንደሆነ ተገልጿል።
በማኒላ ያለው የቻይና ኢምባሲ በበኩሉ የፊሊፒንስ መንግስት ቻይናዊያንን ከሀገሩ ለማባረር የወሰነውን ውሳኔ እንደሚያደንቅ አስታውቋል።