ኢትዮጵያ በጋዝ ፍለጋ ላይ ከነበረው የቻይናው ፖሊ ሲጂኤል ኩባንያ ጋር ያላትን ውል አቋረጠች
ኩባንያው ላለፉት 10 ዓመታት በሶማሊ ክልል ኦጋዴን አካባቢ በነዳጅ ማውጣት ስራ ላይ ነበር
ሚንስቴሩ ከኩባንያው ጋር ውሉን ያቋረጠው የማልማት አቅም የለውም በሚል ነው
የማዕድን ሚንስቴር በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ላይ ከነበረው የቻይናው ፖሊ ሲጂኤል ኩባንያ ጋር ያለውን ውል ማቋረጡን አስታውቋል።
የማዕድን ሚንስትሩ ታከለ ኡማ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላለፉት 12 ዓመታት በሶማሊ ክልል ኦጋዴን አካባቢ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጋዝ ለመፈለግና ለማውጣት ተሰማርቶ ቆይቶ ነበር ብለዋል።
ይሁንና ይህ የቻይና ኩባንያ እንዲያለማ በተሰጠው የፈቃድ ጊዜ ውስጥ የሚጠበቅበትን መስራት አልቻለም ያሉት ሚንስትሩ ኩባንያው የአቅም ችግር እንዳለበት ተገንዝበናል ብለዋል።
ኩባንያው በተለይም የኦጋዴን ነዳጅን ማውጣት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ፣ ገንዘብ እና የሰው ሀይል የአቅም ችግር በማሳየቱ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው የስራ ፈቃድ ስምምነት ከትናንት መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ መቋረጡን ሚንስትሩ ገልጸዋል።
በፖሊሲጂኤል ኩባንያ ላይ የተወሰደው እርምጃ በኢትዮጵያ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብት ማልማት ላይ የተሳተፉ ሌሎች ኩባንያዎችን እንደሚያስተምርም ሚንስትሩ አክለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን በመጡበት 2014 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጣቷን አብረው ነበር።
ኢትዮጵያ በኦጋዴን አካባቢ 7 ትሪሊዮን ኪዪቢክ ጫማ (200 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ) የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መኖሩ የሚያረጋግጥ ጥናት ከአንድ ወር በፊት ይፋ ማድረጓ አይዘነጋም።
ጥናቱ የማዕድን ሚንስቴር ከአሜሪካው ኔዘርላንድ ስዌል ኤንድ አሶሲሼየትስ ኢንክ ኩባንያ (ኤልሲኤአይ) የጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ያስጠናው እንደነበር በወቅቱ ተገልጿል።