ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ዜጎች የሚገደሉት በመንግስት ቸልተኝነት እንዳልሆነ ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው የዜጎችን ህይወት ባለመታደጉ “አዝናለሁ” አሉ

የደህንነትና የጸጥታ ተቋማትን ማጠናከር ግድያዎችን ለማስቆም መፍትሄ ናቸው ተብሏል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፤ አሁን እየደረሰ ያለው ችግር መንግስት ተገቢውን ትኩረት ስላልሰጠ የተከሰተ አለመሆኑን ገለጹ፡፡
መንግስታቸው የዜጎችን ህይወት መታደግ ባለመቻሉ ማዘናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በርካታ የፀጥታ አካላት መስዋዕትነት መክፈላቸውንና እየከፈሉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለዓመቱ የመጨረሻ የሆነውን ማብራሪያ ለፓርላማ አባላት እየሰጡ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላት "መንግስት የዜጎችን ሕይወት ለምን መታደግ አልቻለም፤ ይህ የዜጎች ጭፍጨፋ የሚቆመው መቸ ነው" የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ባልሰሩት ወንጀልና ባልተገባ መንገድ ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎችን መታደግ ባለመቻሉ “ጥልቅ ሃዘን ይሰማናል” ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ጠ/ሚኒስትሩ መንግስታቸው ዜጎችን መታደግ ባመቻሉ ሃዘናቸውን እንደገለጹ ቢናገሩም ዜጎች የሚገደሉት ግን በመንግስት ቸልተኝነት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ሸኔ በሚል የሚጠራውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሚለው ቡድንና ሌሎች ቡድኖች የራሳቸው እግር እንደሌላለቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የትኛውም ስብስብ “ሸኔም ይሁን ሌላ አሸባሪ ሀይል በጀመርነው መንገድ ጉዟችንን አጠናክረን የምንቀጥል ከሆነ ይጠፋሉ” ሲሉም ግድያዎች መቸ ይቆማሉ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ህዝብን የማድመጥ ቀዳሚ ተግባሩ ቢሆንም ህዝብም የመረጠውን መንግስት የማድመጥና የማገዝ ቀዳሚ ተግባር እንዳለውም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ የግራጫ ጦርነት እንዳለ አንስተዋል፡፡
ግድያዎችን ለማስቆም የጸጥታ ተቋማትን ማጠናከር ዋነኛ ስራ መሆን አለበት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።