አብን እየተፈጸሙ ያሉትን "የዘር ማጥፋት" ወንጀሎች የሚመረምር ልዩ አቃቤ ህግ እንዲቋቋም ጠየቀ
አብን የኦሮሞ ልሂቃንና ፖለቲከኞች በአማራ ተወላጆችን ላይ የተፈጸመውን “የዘር ማጥፋት” ወንጀል እንዲያወግዙት ጠየቀ
አብን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅና የፌደራል የጸጥታ ኃይል እንዲሰማራም ጠይቋል
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ጥቃት "ዘር ማጥፋት ብሎታል።
የአብን ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና የንቅናቄው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር መሐመድ ፤ በአማራ ተወላጆች ላይ በተፈጸመው “የዘር ማጥፋት” ዙሪያ ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አብን፤ በኦሮሚያ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀሙ “የዘር ማጥፋት” ወንጀሎች የሚመረምር ልዩ አቃቤ ህግ በአዋጅ እንዲቋቋም ጠይቋል፡፡ ይህንን ተከትሎም የወንጀል ፈፃሚዎች በግልፅ ችሎት መዳኘት እንዳለባቸው ንቅናቄው ጠይቋል፡፡
የፓርቲው ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ፤ በአማራ ሕዝብ ላይ ባለፉት ዓመታት የተሰራው የተሳሳተ ትርክት አሁን ለሚካሄደው “የዘር ማጥፋት ወንጀል” ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የንቅናቄው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር መሐመድ፤ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት እየተጨፈጨፉ ባሉባቸው የወለጋ ዞኖች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ጣሂር ፤ ሕግ አውጭው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን እንዲያውጅና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎችም በአካባቢው እንዲሰማሩ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
“የዘር ማጥፋት” ወንጀሉ ሰለባዎች ራሳቸውን እንዲከላከሉ ሊደረግ እንደሚገባም ነው ንቅናቄው የጠየቀው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ማንነት ላይ ያተኮረ ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ቅስቀሳ ሲያደርጉ እና እያደረጉ ያሉ አካላት እንዳሉም ነው ፓርቲው በመግለጫው የጠየቀው፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ የመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት በዚህ ውስጥ እጃቸው ቢኖርበትም በጅምላ ግን እነዚህ ናቸው ማለት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ያስተላለፈው ውሳኔ ለአማራ ሕዝብ ያለውን ንቀት ያሳየበት ነው ሲልም ነው አብን የገለጸው፡፡ ከዚህ ባለፈም “የብሔር፣ ብሔረሰቦች ጠበቃ” እንደሆነ የሚገልጸው የፌዴሬሽን ም/ቤትም ይህንን ችግር ባለማስቆሙ “የዘር ማጥፋት ወንጀሉ” ተባባሪ ነው ሲል ንቅናቄው ከሷል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ በቀጣይ ሀሙስ ባልታጠቁ ዜጎች (ሲቪሊያን) ላይ የተፈጸመውን “የዘር ማጥፋት” ወንጀል በሁሉም መዋቅሮቹ በተለያዩ መርሃ ግብሮች አስቦት እንደሚውል አስታውቋል፡፡
አብን የኦሮሞ ልሂቃንና ፖለቲከኞች ለኦሮሞ ህዝብ ክብር ሲሉ በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን "የዘር ማጥፋት" ወንጀል እንዲያወግዙት ጠይቋል።
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምእራብቅ ወለጋ በርካታ ንጽሃን ዜጎች ተገድለዋል፤ ግድያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት አውግዘውታል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ግድያው በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ነው ማለቱ ይታወሳል።