የጥር የዝውውር መስኮት ወጪ ከባለፈው አመት ጋር ሲንጸጸር ከእጥፍ በላይ መጨመሩ ተነገረ
የዝውውር መስኮቱ ሊዘጋ አንድ ሳምንት ሲቀረው እስካሁን 247 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ ተደርጓል
ለአጠቃላይ ለተጫዋቾች ዝውውር ከወጣው ወጪ ግማሹን የሚሸፍነው የአምናው ሻምፒዮና ማንችስተር ሲቲ ነው
በጥር የዝውውር መስኮት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የተጫዋቾች ዝውውር ወጪ ከባለፈው አመት ጋር ሲንጸጸር ከእጥፍ በላይ መጨመሩ ተሰምቷል፡፡
የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በዚህ አመት ወጪ ያደረጉት 247 ሚሊየን ፓውንድ ከባለፈው አመት ከወጣው አጠቃላይ 90 ሚሊየን ፓውንድ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ የታየበት ነው፡፡
የዝውውር መስኮቱ ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ክፍት ሆኖ መቆየቱን ተከትሎ ተጨማሪ የሚጠናቀቁ የተጫዋች ግዢዎች ወጪው ከዚህም ከፍ እንዲል ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡
በጥር የዝውውር መስኮት ከፍተኛ የተጫዋቾች ዝውውር ወጪ ክብረወሰን የተያዘበት አመት 2023 ሲሆን በዚህ ጊዜ 815 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ ተደርጎ ነበር፡፡
የፉትቦል ትራንስፈር ዶት ኮም መረጃ እንደሚያመላክተው የአምናው ሻምፒዮና ማንችስተር ሲቲ 125 ሚሊየን ፓውንድ ለተጫዋቾች ዝውውውር በማውጣት በሊጉ በአጠቃላይ የወጣውን ወጪ ግማሽ ያህሉን ይሸፍናል፡፡
ምንም እንኳን ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወጪ ፒኤስጂ የናፖሊውን ኮከብ ኽቪቻ ክቫራትክሄሊያን በ59 ሚሊዮን ፓውንድ ያስፈረመበት ቢሆንም ፤ሊግ 1 በዚህ ወር በ106 ሚሊየን ፓውንድ ቀጣዩ ከፍተኛ ወጪ ያወጣ ሊግ ነው፡፡
ማንችስተር ሲቲ የፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ክብሩን ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ደካማ እንቅስቃሴ እያሳየ መሆኑን ተከትሎ ጋርዲዮላ በከፍተኛ ገንዘብ 3 ዝውውሮችን አከናውኗል፡፡
ሲቲ የኢንትራክት ፍራንክፈርቱን አጥቂ ኦማር ማርሙሽ (59 ሚሊየን ፓውንድ)፣ የፓልሜራስ ተከላካይ ቪቶር ሬስን (በ29.6ሚሊየን ፓውንድ) እና የሌንስ የመሀል ተከላካይ አብዱኮድር ኩሳኖቭን (በ33.6ሚሊየን ፓውንድ) አስፈርሟል።
ሊቨርፑል በበኩሉ በጥር የዝውውር መስኮት ከመሳተፍ ይልቅ ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ፣ ቨርጂል ቫን ዳይክ እና የመሀመድ ሳላህ ኮንትራትን ማራዘም ላይ ሊያተኩር ይችላል ተብሏል፡፡
ከማንችስተር ሲቲ ባለፈ በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል ወደ ሊግ ላለመውረድ የሚታገለው ኢፕስዊች እና ሳውዝሃምፕተን እያንዳንዳቸው ሶስት ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡
ቶትንሀም ፣ ብራይተን ፣ክሪስታል ፓላስ እና ዎልቭስ በዝውውር መስኮት እየተሳተፉ የሚገኙ ሌሎች ቡድኖች ናቸው፡፡
በአንጻሩ ሊቨርፑል፣ አርሰናል፣ ቼልሲ እና ማንችስተር ዩናይትድን ጨምሮ ሌሎች 8 ቡድኖች እስካሁን ምንም ተጫዋች አላስፈረሙም፡፡
አሁንም ብዙ ፊርማዎች የሚጠበቁ ሲሆን ማንቸስተር ዩናይትድ ከሩበን አሞሪም ቡድን ስብስብ ውጪ ለሆነው እንግሊዛዊው አጥቂ ማርከስ ራሽፎርድ አዲስ ክለብ ለማግኘት እየሞከረ ነው፡፡
የክንፋ ተጫዋቹ አሌሃንድሮ ጋርናቾ ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል በሚነገርበት ወቅት ቼልሲ እና ናፖሊ ከተጫዋቹ ጋር ተያይዞ ስማቸው አብሮ እየተነሳ ነው።
የዩናይትድ እነዚህን ተጫዋቾች መሸጥ ወደ ሊጉ ሰንጠርዥ አጋማሽ ለመጠጋት የሚያግዙትን ተጫዋቾች ለማስፈርም የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው፡፡
በርካታ የአጥቂ መሰመር ቁልፍ ተጫዋቾቹ የተጎዱበት አርሰናል በተመሳሳይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል አጥቂ ለማስፈረም በማፈላለግ ላይ ይገኛል፡፡