ስፖርት
አቡበከር ናስር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብረ ወሰንን በእጁ አስገባ
አቡበከር ዛሬ 3 ጎሎችን በማቆጠር በውድድር ዘመኑ ከመረብ ያሳረፋቸውን ጎሎች ቁጥር 27 አድርሷል
የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አግቢነትን ጌታነህ ከበደ በ2009 የውድድር ዘመን በ25 ጎሎች ይዞ ነበር
የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምንጊዜም ከፍተኛ አግቢነት ክብረ ወሰንን በእጁ አስገባ።
አቡበከር ናስር በዛሬው እለት ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ነው ክብረ ወሰኑን በእጁ ማስገባቱን ያረጋገጠው።
ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ጋር በዛሬው እለት ያደረጉት ጨዋታ 3 አቻ በሆነ ወጤት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ቡና 3 ጎሎችን አጥቂው አቡበከር ናስር ነው ከመረብ ያሳረፈው።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ በውድድር ዘመኑ ከመረብ ያሳረፋቸውን ጎሎች ቁጥር 27 ማድረስ ችሏል።
በዚህም ከወዲሁ በጌታነህ ከበደ በ2009 ተይዞ የነበረውን በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል የማስቆጠር ክብረ ወሰንን ማሻሻል ችሏል።
ጌታነህ ከበደ በ2009 የውድድር ዘመን ለደደቢት 25 ግቦችን በማስቆጠር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብረወሰንን ይዞ መቆየቱ ይታወሳል።
ጌታነህ ከበደ ክብረወሰኑን በእጁ ከማስገባቱ በፊት ዮርዳኖስ ዓባይ በ24 ግቦች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምንጊዜም ከፍተኛ አግቢነት ክብረወሰንን ይዞ እንደነበረም አይዘነጋም።