ኤርሊንግ ሀላንድ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ረጅሙን ኮንትራት ተፈራረመ
የማንችስተር ሲቲው አጥቂ ከቡድኑ ጋር ለ9 አመት ተኩል የሚያቆየውን የውል ማራዘሚያ ፈርሟል
ከ2022 ጀምሮ ሲቲን የተቀላቀለው ሀላንድ በ116 ጨዋታዎች 111 ገቦችን አስቆጥሯል
የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኤርሊንግ ሃላንድ በኢትሃድ እስከ 2034 ድረስ የሚያቆየውን አዲስ የረጅም ጊዜ ውል ተፈራርሟል ።
በ2022 ከዶርትሙንድ ሲቲን የተቀላቀለው ኖርዌያዊው አጥቂ የውል ማፍረሻን ያካተተው ቀደም ሲል የተፈራረመው ስምምነት በ2027 ይጠናቀቃል፡፡
የሃላንድ አዲስ ውል እስከ 34ኛ አመቱ ድረስ በሲቲ የሚያቆይ ሲሆን ውሉ በአጠቃላይ ለ9 አመት ተኩል ጊዜ የሚዘልቅ ነው፡፡
ስምምነቱ ኮል ፓልመር ከቼልሲ ጋር ባለፈው ነሀሴ የተፈራረመውን የዘጠኝ አመት ውል በመብለጥ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ረጅሙ እንደሚሆን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተጫዋቹ ከፊርማው በኋላ ባደረገው ንግግር "ማንቸስተር ሲቲ አስደናቂ ደጋፊዎች እና ድንቅ ሰዎች የሚገኙበት ሁሉም ሰው የተሻለ አቅም እንዲኖር የሚረዳ ካባቢ ያለው ልዩ ክለብ ነው” ብሏል፡፡
አክሎም “አዲሱን ኮንትራቴን በመፈረሜ እና በዚህ ታላቅ ክለብ ረጅም ጊዜ ማሳለፍ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ” ነው ያለው::
የሲቲ የእግር ኳስ ዳይሬክተር ቲኪ ቤጊሪስታይን በበኩላቸው “ሀላንድ ለረጅም ጊዜ መፈረሙ በተጫዋቹ ላይ ያለንን እምነት እና እሱም ለክለቡ ያለውን ፍቅር ያሳያል” ብለዋል።
ኖርዌያዊው አጥቂ በኢትሀድ በቆየባቸው አራት አመታት በ116 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 111 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
ሀላንድ ለሲቲ በተሰለፈባቸው ሁሉም ጨዋታዎች በሚባል ደረጃ ጎል ያስቆጠረ ሲሆን በሻምፒዮንስ ሊግ በ92 ደቂቃዎች ፣ በኤፍኤካፕ ደግሞ በ72 ደቂቃ ልዩነት ጎል አስቆጥሯል፡፡
በ2022-23 በሲቲ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን ቆይታው በሁሉም ውድድሮች 52 ጎሎችን (በየ79 ደቂቃው አንድ ግብ) ማስቆጠር ችሏል።
ባለፈው የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች 38 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው ተጫዋቹ በዘንድሮው አመት 22 ጎሎችን ብቻ ነው ያስቆጠረው፡፡
በሲቲ የፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ 184 ግብ ካስቆጠረው አጉዌሮ እና ከራሂም ስተርሊንግ 91 ገቦች ቀጥሎ በ79 ግብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሃላንድ በፕሪምየር ሊግ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ደግሞ 61ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡