የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በአስመራ ጉብኝት አደረጉ
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን የአካባቢውን ፖለቲካ የሚተንትኑ ሰዎች ያነሳሉ፡፡
ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የመሪዎቻቸው የእርስ በእርስ መቀራረብና የስራ ጉብኝቶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ወደ ሃላፊነት ከመጡ ወዲህ እንኳን ወደ ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በቀጣናው ሀገራት መካከል የነበረው ግንኙነት እንዲጠናከር ሲያደርጉ እንደነበርም እንዲሁ፡፡
ይህም ቀጣናው ይታወቅበት ከነበረው የግጭትና የተኩስ ድባብ እንዲወጣ ያደርገዋል የሚል ትልቅ ተስፋ አጭሯል፡፡
ባለፈው ወር የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአዲስ አበባ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል ይህም ለኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ (ፋርማጆ) ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመራ መግባታቸውን የኤርትራ መንግስ አስታወቋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አስመራ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ማድረጋቸውን የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህ ጉብኝት ሞቃዲሾና አስመራን በጋራ እንዲሰሩ፣ እንዲለሙና እንዲተሳሰሩ በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
የሁለቱ ሀገሮች መሪዎች በአስመራ በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
በዋናነትም ሰላምና ጸጥታ፣ መከላከያ ዘርፍ፣ ኢኮኖሚና መሰረተ ልማት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የሶማሊያ አቻቸው መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የተወያዩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው ተብሏል፡፡
ሁለቱም መሪዎች በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መካከል በተደረገው የሦስትዮሽ ስምምነት ደስተኞች መሆናቸውንና ይህም ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸል፡፡