ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ
በኢትዮጵያ ረጅም የፖለቲካ ተሳትፎ በነበራቸው ፕሮፌሰር በየነ ህልፈት ከልብ ማዘናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገልጸዋል
ፕሮፌሰር በየነ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመመስረት ለረጅም አመታት ሲታገሉ የቆዩት ፕሮፌሰር በየነ ባደረባቸው ህመም ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
“ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮዽያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።
በፕሮፌሰር በየነ ህልፈት ከልብ ማዘናቸውን በመግለጽም “ያቆዩት ውርስ እና ቅርስ ፀንቶ እንዲቀጥል ነፍሳቸውም በሰላም እንድታርፍ እመኛለሁ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)ን በፕሬዚዳንት የመሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፥ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸውም ይታወሳል።
ፖለቲከኛ፤ የስነህይወት ምሁር
በ1942 ዓ.ም ሃድያ ዞን የተወለዱት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፥ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኛነት ከሚነሱት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
በሽግግሩ የደቡብ ፓርቲዎችን አስተባብረው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲ ህብረት የተባለ የፖለቲካ ድርጅት በመመስረት 17 መቀመጫ ይዘው እንደነበር ይታወሳል።
በኢህአዴግ አስተባባሪነት በተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ለሁለት ዓመት ያገለገሉት ፕሮፌሰር በየነ፥ በ1992 ዓ.ም በሁለተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተወዳድው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም ሆነው ነበር።
ፕሮፌሰር በየነ ቁጥራቸው የበዛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ፈጥረው ተጽእኖ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ይነገርላቸዋል።
በ1997 ምርጫ ከቅንጅት ጋር ዋነኛ ተፎካካሪ የነበረውን ህብረት እንዲሁም ከዚያ በኋላ መድረክ የተባሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትን ካቀቋሙ ቁልፍ ፖለቲከኞች መካከል ይጠቀሳሉ።
በ1965 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በስነ ሕይወት አግኝተዋል።
የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካው ዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ የተቀበሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከቱሊን ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውም ይታወሳል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሕዝብ ተሳትፎ፣ በአካዳሚክ ውጤታቸው እና በምርምር መሪነት በርካታ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ሽልማቶችን እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችለዋል።
ምሁሩ በየነ ጴጥሮስ በሙያቸው ወደ 120 የሚጠጉ በአቻ የተገመገሙ ሳይንሳዊ የጥናት ጽሁፎችን በጥናታዊ መጽሔቶች ላይ በማሳተምም ልሂቅነታቸውን አስመስክረዋል።