በፍሎሪዳው የትራምፕ የግድያ ሙከራ የተጠረጠረው ግለሰብ ማን ነው?
ሪያን ዌስሊ ሩት የተባለው የ58 አመት ጎልማሳ ለዩክሬን የውጭ ሀገር ተዋጊዎችን ሲመለምል ቆይቷል ተብሏል
በህዳሩ ወር ምርጫ ሪፐብሊካኖችን የሚወክሉት ትራምፕ በሁለት ወር ውስጥ ሁለት የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸዋል
በዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ የተጠረጠረው ግለሰብ ማንነት ይፋ ተደርጓል።
የአሜሪካው ሲቢኤስ በሪፐብሊካኑ እጩ ፕሬዝዳንት ላይ የግድያ ሙከራውን ያደረገው ሪያን ዌስሊ ሩት መሆኑን ዘግቧል።
የ58 አመቱ ጎልማሳ ዩክሬንን የሚደግፍ ማህበረሰብ አንቂ (አክቲቪስት) መሆኑንም ነው ዘገባው የጠቀሰው።
የሃዋይ ነዋሪው ተጠርጣሪ ወደ ዩክሬን በመዝመት የሚዋጉ የውጭ ሀገር ወታደሮችን ሲመለምል መቆየቱና ወደ ኬቭም ደጋግሞ መጓዙ ተገልጿል።
ሩት በ2023 ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት እንደከፈተች (በ2022) ወደ ኬቭ ማቅናቱን ተናግሯል። በወቅቱም ከታሊባን የወጡ አፍጋኒስታናውያን ወታደሮች ለዩክሬን ተሰልፈው እንዲዋጉ የመመልመል ሃሳብ አቅርቦ ነበር ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ተጠያቂው የባይደን አስተዳደር መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
በህዳሩ ወር ምርጫ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ የሚያስገባ ውጤት ካገኙም የዩክሬኑን ጦርነት በአንድ ቀን እንደሚያስቆሙት መግለጻቸው አይዘነጋም።
የዩክሬን ደጋፊ ነው የተባለው ሪያን ዌስሊ ሩት በፍሎሪዳ በሚገኘው የትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ የግድያ ሙከራውን ያደረገው ለምንድን ነው? የሚለውን የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ምርመራ እያደረገበት ነው።
የፍሎሪዳ ግዛት ፖሊስም ከዚህ ቀደም በወንጀል ሲፈለግ የነበረውን የሩት ቤት መበርበሩን ቢቢሲ ዘግቧል።
“በርካታ የተሰረቁ ንብረቶችን በምድር ቤት ሲደብቅ ነበር” የሚሉት ጎረቤቱም ፥ ሩትና ቤተሰቦቹ በተደጋጋሚ የጦር መሳሪያዎችን ይዘው ሲወጡ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የ58 አመቱ ጎልማሳ ክላሽንኮቭ መሰል መሳሪያ ታጥቆ ከጫካ ውስጥ በመተኮስ በትራምፕ ላይ የፈጸመው የግድያ ሙከራ በአሜሪካ ሚስጢራዊ ደህንነት አባላት (ሴክሬት ሰርቪስ) መክሸፉን ኤፍቢአይ ገልጿል።
ተጠርጣሪው ከተኩስ ልውውጡ በኋላ በተሽከርካሪ ለማምለጥ ሞክሮ ከ61 ኪሎሜትሮች ማሳደድ በኋላ መያዙም ነው የተዘገበው።
በሁለት ወራት ውስጥ ሁለተኛው የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ትራምፕ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም፤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸውም “ደህና ነኝ፤ ምንም ነገር ቢመጣ ወደኋላ አይመልሰኝም፤ በፍፁም እጄን አልሰጥም” ብለዋል።
ትራምፕ በፈረንጆቹ ሃምሌ 13 በፔንሲልቫኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ መትረፋቸው ይታወሳል።