የቬንዝዌላውን ፕሬዝዳንት ለመግደል አሲረዋል የተባሉ 6 የውጭ ሀገር ዜጎች ታሰሩ
ፖሊስ ከተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ የጦር መሳርያ እና የግድያ እቅድ አግኝቻለሁ ብሏል
ተጠርጣሪዎቹ ፕሬዝዳንቱን ለመገደል እና የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ ከሲአይኤ ተልዕኮ እንደተቀበሉ ተነግሯል
የቬንዝዌላውን ፕሬዝዳንት ለመግደል አሲረዋል የተባሉ 6 የውጭ ሀገር ዜጎች ታሰሩ።
የቬንቪዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ለመግደል ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ 6 የውጭ ሀገር ዜጎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል፡፡
3 የአሜሪካ ፣ 2 የስፔን እና አንድ የቼክ ሪፐብሊክ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ የተለያዩ በከፍተኛ አመራር ቦታ ላይ የሚገኙ ባለስልጣናትን ለመግድል እያሴሩ እንደነበር የቬንዝዌላ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ዲዮስዳዶ ካቤሎ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
ግለሰቦቹ ፕሬዝዳንቱን በመግደል የመፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ከአሜሪካ የስለላ ተቋም ሴአይኤ ተልዕኮ ተቀብለው ከደቡብ አሜሪካ ሀገራት እንደገቡ ነው ሚንስትሩ በመግለጫው ላይ የገለጹት፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሁለቱ በአሜሪካ ባህር ሀይል ስር በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ጦርነቶች የተሳተፉ የጦርነት ልምድ ያላቸው ወታደሮች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
በቬንዝዌላ ዜጎቹ እንደታሰሩ ማረጋጋጫ የሰጠው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መንግስትን ለመገልበጥ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል ተብሎ የቀረበባቸውን ክሶች አጣጥሏል፡፡
ሚንስትሩ ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ ለሚገኘው ፖለቲካዊ ቀውስ አሜሪካ ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ እንዲበጅለት ከመደገፍ በዘለለ አመጽ እና ብጥብጥ መፍትሄ ነው ብላ አታምንም ብሏል፡፡
በግድያ ሙከራ 6 የውጭ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተሰማው የአሜሪካ ግምጃ ቤት የምርጫ ሂደቱን በማስተጓጎል እና ሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ በመሳተፍ የፕሬዝዳት ማዱሮ አጋር ናቸው ባላቸው 16 ሰዎች ላይ ማዕቀብ ካሳለፈ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው፡፡
በፈረንጆቹ ሀምሌ 28 በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ ፕሬዝዳንት ማዱሮ እንዳሸነፉ ቢገለጽም በተቀናቃኞቻቸው እና በምዕራባውያን ዘንድ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል እውቅና ተነፍጎታል፡፡
በሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የስፔን ፓርላማ የማዱሮ ተቀናቃኝ የነበሩትን ኤድሞንዶ ጎንዛሌዝ የዘንድሮው ምርጫ አሸናፊ ናቸው በሚል እውቅና ሰጥቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ የምርጫ ውጤቱን በመቃወም በሀገሪቱ በተከታታይ በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች የተለያዩ የማህበረሰብ አንቂዎች እና ፖለቲከኞች ለእስር ተዳርገዋል፡፡
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዝርዝር ውጤቶችን ይፋ ባላደረገበት መግለጫው ማዱሮ 52 በመቶ በሆነ ውጤት ምርጫውን ማሸነፋቸውን አውጇል፡፡
ከ2013 ጀምሮ በቬንዝዌላ መንበር ላይ የሚገኙት ማዱሮ ከአሜሪካ ጋር በሚገኙበት ውጥረት ሀገሪቱ በማዕቀብ እና በስውር ዘመቻዎች ከስልጣን ልታስወግደኝ ሞክራለች በሚል ተደጋጋሚ ክስ ያቀርባሉ፡፡