የብልጽግና ፓርቲው አቶ ዛዲግ፡ “በዚህ ምርጫ በፍጹም የመንግስትን ንብረት አንጠቀምም”
“ለምርጫ ሲባል ፖለቲከኞችን ማሰር ከቆመ ሦስት ዓመት አልፎታል…”፡ አቶ ዛዲግ አብርሃ
አቶ ዛዲግ ብልጽግና ፓርቲ “ማንኛውም ዋጋ ከፍዬ ምርጫውን አሸንፋለሁ” ብሎ አይንቀሳቀስም ብለዋል
አል ዐይን አማርኛ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ ጋር ቆይታ አድርጓዋል፡፡ አቶ ዛድግ በቆይታቸው ሀገራዊ ምርጫና የጸጥታ ሁኔታ እንዲሁም በውህደት ስለተመሰረተው የብልጽግና ፓርቲ ሕጋዊነት በተመለከተ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ሙሉ ቃለ ምልልሱን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ውህድ ፓርቲ መሆኑን ቢገልጽም አሁንም በየክልሎቹ ስም ብልጽግና እንጅ ቅርንጫፍ የሚል ነገር የለውም፡፡ በመሆኑም አሁን ያለው የብልጽግና ፓርቲ ሁኔታ ልክ እንደ ቀደመው የኢህአዴግ ግንባር አወቃቀር ነው የሚመስለው ይባላል፡፡ በዚህ ሁኔታ በትክክል ብልጽግና ውህድ ሀገራዊ ፓርቲ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ዛዲግ ፡- አንድ ፓርቲ ተዋሃደ ወይም አልተዋሃደም ስትል እንግዲህ መጀመሪያ የሚታየው ፕሮግራም ነው፡፡ ፕሮግራሙ አንድ አይነት ነወይ? ብልጽግና አንድ አይት ፕሮግራም ያለው ፓርቲ ነው፡፡ ከዛ ደግሞ የሕግ ጥያቄ ነው፡፡ ተዋህዷል ማለት አንድ ፓርቲ ሆኖ ምርጫ ቦርድ መዝግቦታል ወይ የነበሩት ፓርቲዎች ደግሞ እኛ ያው ግንባር የነበርን ስለሆንን ከስመዋል ወይ ምናምን ነው የሕግ ጥያቄ ነው፤ምርጫ ቦርድን መጠየቅ ትችላለህ ከስመዋል፡፡ ስለዚህ በግብርም አንድ ፕሮግራም ያለን፤ በሕግ ስናወራም በምርጫ ቦርድ እንደ አንድ ፓርቲ የነበሩት ፓርቲዎች ከስመው አንድ ፓርቲ የተቋቋመበት ፓርቲ ነው፤ ውህድ ነን፤ግን ከተዋሃድን ገና አንድ ዓመታችን ነው ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ይህንን በደንብ ማየትና ማስረጽ ይገባል፡፡ ከዛ ውጭ ግን ሁሉም ፓርቲ ተሰብስቦ ወስኖ ያደረገው ነገር ነው፡፡ ከውህደቱ እንጠቀማለን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይጠቀማል፤፡፡ የመሃል ፖለቲካ የሳሳ ፖለቲካ ነው፤ ፖለቲካችን በዋልታ ረገጥ ችግር ውስጥ ተወጥሯል፡፡ ዋልታ ረገጥነት አይነተኛ የፖለቲካችን መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህ በመሃል ፖለቲካ የሚያምን አንድ ውህድ ፓርቲ ብናቋቁም የሀገራችንን ሕዝቦች ከብዙ ችግር እንታደጋለን የሚል ጠንካራ እምነት የወለደው ፓርቲ ነው እና ብልጽግና በሕግ ቋንቋም በግብርም የተዋሃደ ነው፡፡ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አሉት፡፡ እነዛ ጽ/ቤት ስራቸውን እየሰሩ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ግን በየክልሉ ስም ብልጽግና ተብለው ነው ሥያሜያቸው የሚታየው ቅርንጫፍ አይልም?
አቶ ዛዲግ ፡- ለአጠራር እንደሚመች ሆኖ ሊጠራ ይችላል፤ ዞሮ ዞሮ አንድ ፓርቲ ውህድ ነው አይደለም የምትለው የፕሮግራም አንድነት አለው ወይ፤ በሕግስ አንጻር አንድ ፓርቲ ሆኖ ተቋቁሟል ወይ ነው እና ብልጽግና ከባዱን ምዕራፍ የተሻገረ ነው፤እነዛ የራሳቸው ኢምፓየር የነበራቸው ፓርቲዎች ፈርሰው በምትኩ አንድ ውህድ ፓርቲ ተፈጥሯል እና የሄድንበት ርቀት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ተዋህዷል አልተዋሃደም ብሎ አሁን በዚህ ሰዓት ማንሳትም አንድ እውነታን መጻረር ነው፤ጉንጭ አልፋ ክርክር ነው ምክንያቱም መዋሃዱን ሁላችንም የምናውቀው ነገር ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- አንዱ የዚህ ጥያቄ መነሻ ጉባዔዎችን አላደረጋችሁም የሚል ነው፡፡ ብልጽግና ለምን ጉባዔ አላደረገም?
አቶ ዛዲግ ፡- በሕጉ መሰረት በዚህ ጊዜ ጉባዔ ማድረግ ያልቻሉ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ፈቅዶልን በባለፈው ጉባዔ የነበረው አመራር ጊዜያዊ ሆኖ እንዲቀጥልና ምርጫ በተካሄደ በሦስት ወር ውስጥ ጉባዔ እንድናደርግ እና ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ፓርቲዎች ጥያቄ አቅርበው ተፈቅዶላቸው ነው እየሄድን ያለነው፡፡ ስለዚህ ይቻላል አንደኛ ዴሊጌሽን ነበረው የባለፈው የኢህአዴግ ጉባዔ የሕግ ሂደቱን ያሟላል፡፡ ግን ደግሞ ጉባዔ ቶሎ ብለን ማድረግ የምንፈልግ ፓርቲ ነን በርካታ ነገሮች አጋጥመውን ነው እንጅ ለነገ ለዛሬ ብለን ማስተላለፍ የምንፈልገው ነገር አይለም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የንጹሃን ግድያዎችን፤ መፈናቀሎችንና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፍተኛ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸው በተለያዩ መንገዶች ይሰማል፡፡
አቶ ዛዲግ፡- ብልጽግና እንደ ኢህአዴግ አይደለም፤ ልዩነት ሲኖር በነጻነት መከራከር፤ መነጋገር ችግር የሌለበት ፓርቲ ነው፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ፓርቲ እኛ ፓርቲ ውስጥ የተለያየ ሀሳብ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ የጤናማነት ምልክት ነው፤ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲም መገለጫ ነው፤ ከዛ በዘለለ ግን አሁን የሚነገረው ነገር ፓርቲያችን ውስጥ የለም፡፡ መለስተኛ ልዩነቶች በማንኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም ፓርቲ፤የአሜሪከም፣የእንግለዝም ፓርቲ ውስጥ ሊኖር የሚችል ነገር ነው፡፡ እስካሁን ግን ተወያይተን፤ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተን መጨረሻ ላይ በድምጽ ብልጫ እየተወሰነ በጋራ እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው፡፡ አመራሮች ነንና ይህን ብልጽግናን አይገልጸውም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ብልጽግና ለዚህ ምርጫ የመንግስትን ገንዘብና ንብረት ይጠቀማል?
አቶ ዛዲግ፡- ወደዚህ ምርጫ ስንገባ ሁለት ነገር በግልጽ አስቀምጠናል፤ ካሸነፍን ፕሮግራማችንን የሚፈጽምልን እናገኛለን፤ ከተሸነፍን በታሪክ በዚህ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ተሸንፎ ስልጣኑን ያስረከበ ፓርቲ እሆናለን ብለን ወስነን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ምርጫ ለማሸነፍ የምናጭበረብረው ነገር ፤ የመንግስትን ሀብት የምንመዘብረው ነገር አይኖርም፤ መኪና ሁሉ እየገዛን ነው የራሳችን መኪና፤ የነበሩን መኪኖች በቂ ስላልሆኑ እየገዛን ነው፤ ስለዚህ በፍጹም የመንግስትን ንብረት አንጠቀምም፡፡ በእኩልና በፍትሐዊነት ተወዳድረን ማሸነፍ እንፈልጋለን፤ ሀሳባችን ለማሸነፍ በቂ ነው ብለን እናምናለን፤ ያለን ግዙፍ መዋቅር ምርጫውን ለማሸነፍ በቂ ነው ብለን እናስባለን፤ በዛ ምክንያት ወደሌላ ነገር አንገባም፤ይሁንና እሱ ሁሉ በቂ ሳይሆን ብንሸነፍ በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን ስለዚህ ወደዛ አይነት ነገር አንገባም፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣው የምርጫ ሥነምግባር ደንብ ቢኖርም ያ ብቻ በቂ አይደለም ብለን ከፍተኛ ደረጃ ያለው የውስጠ ፓርቲ የምርጫ ስነምግባር ደንብ አዘጋጅተን እሱን ወደማሰልጠን እየገባን ነው፡፡ ስለዚህ በጥብቅ ዲሲፕሊን እናስፈጽማለን፤መጀመሪያ በሁሉም አመራርና አባላት ዘንድ ግንዛቤ እንፈጥራለን፤ ከዛ ደግሞ እንፎካከራለን፡፡ ሥነምግባሩን ጥሶ የተገኘ አባላችን ላይ እርምጃ እንወስዳለን፤ስለዚህ በዚህ ደረጃ ቢያዝ ጥሩ ነው፡፡ በዝግጅት ረገድ የምርጫ ምልክታችንን አስመዝግበናል፤ የሰነድ ዝግጅትና የአጸዳደቅ ሂደቱን ጨርሰናል፤ የዕጩ ምልመላም በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን፤ በአጠቃላይ በዚህ ምርጫ አቅማችን በፈቀደው ሁሉ ለመፎካከር ዝግጁ ሆነን ነው እየገባን ያለነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ምን ምልክት መረጣችሁ?
አቶ ዛዲግ፡- ምርጫ ቦርድ ሲያጸድቅልን ብናሳውቃችሁ ይሻላል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የተለየ ምርጫ ነው ልንለው እንችላለን? ምን ያህል አባላት አሏችሁ?
አቶ ዛዲግ፡- ወደ 9 ሚሊዬን ገደማ የሚሆኑ አባላት አሉን፡፡ የተለየ ምርጫ ነው በእርግጥ፡፡ ይህ የሚሆንበት የተለያየ ምክንያት አለው፡፡ አንደኛው ገዢው ፓርቲ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ማንኛውም ዋጋ ከፍዬ ምርጫውን አሸንፋለሁ ብሎ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ አይደለም አሁን፡፡ ማሸነፍን ብቻ አስቦ ወደ ምርጫ የሚገባ ፓርቲ አይደለም፡፡ ባሸንፍስ ብሸነፍስ ብሎ አስቦ ብሸነፍ ምንድነው የማደረግው ብሎ ወስኖ የህዝብን ውሳኔ ለማክበር እና ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ብሎ እየገባ ያለ ፓርቲ ነው፡፡
ለምን ገዥው ፓርቲ ግዙፍ ስለሆነ አቅም ስላለው የመንግስት ስልጣን ስለተቆናጠጠ ረባሹ እሱ ነው፤ ዋናው ሊሆን የሚችለው፡፡ እሱን መሰረታዊውን ነገር ቀይረናል፡፡ ከዚያ ደግሞ የምርጫ ተቋማቶቻችን ናቸው፡፡
እነ ምርጫ ቦርድ ከአሁን በፊት ምን ይነሳባቸው እንደነበር እና አሁን ማን እንደሚመራቸው ይታወቃል፡፡ ፍርድ ቤት፣ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማን እንደሚመራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ተቋማት ይመደብላቸው የነበረው ውስን ሃብት የሰው ሃይላቸው ይታወቃል፡፡ አሁን በመሰረቱ ተቀይሯል፡፡ ከዚህ በፊት ተቃዋሚዎች ውጭ ሆነው ሚዲያ ታግዶ ነበር ምርጫ የሚደረገው፡፡ይሄ ሁሉ ቀርቷል፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ የዳኝነት ተቋማቱ ምርጫ ቦርዱ፣ ዳኝነቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ነጻ ሆነው ተደራጅተዋል፡፡ እኛ [ገዥው] ፓርቲ ተቀይረናል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝቡ የበለጠ ከፍተኛ የሆነ የነጻነት ስሜት ይሰማዋል፤ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል፡፡በዚህ አውድ የሚደረግ ምርጫ ደግሞ እውነትም ልዩ ምርጫ ነው፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ልዩ ምርጫ መሆኑ ምንም ጥርጥር ውስጥ አይገባም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰላምና መረጋጋት የለም፡፡ ወለጋ፣መተከል እና ሌሎችንም መጥቀስ እንችላለን፡፡ ይሄን እንዴት ባለ መልኩ ልታጣጥሙት አስባችኋል?
አቶ ዛዲግ፡- እነዚህ አካባቢዎች ግጭት እንዳለ እናውቃለን፡፡ ያሳስበናል የህዝባችን ሁኔታ፡፡ እነዚህ አካባቢዎች የሚገኘው ህዝባችን ጉዳት እንደደረሰበት እናውቃለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተሰማንን ሃዘን ለመግለጽ እንፈልጋለን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡
ምርጫው ከመደረጉ በፊት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፤ የጸጥታ ችግር ያለባቸው ቦታዎች ትኩረት ሰጥተን በተለየ ጣልቃ ገብነት ሰላም እንዲከበር የማድረግ እቅድ አውጥተን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
ለዚህም ምርጫ ቦርድ የሚመራው የጸጥታ እና ደህንነት ሁኔታውን የምርጫውን ሰላማዊነት የሚከታተል ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
ኮሚቴው የተሟላ ጸጥታ ያለባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዳይደፈርስ፤ የተለየ ችግር ያለባቸው ቦታዎች ደግሞ በልዩ ዕቅድ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ፣ ድምጻቸውን የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ በህዝባችን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ፣ ዳግም አለመረጋጋት እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የታሰሩ የፖለቲካ አመራሮች አሉ፡፡ እነሱ በታሰሩበት ሁኔታ እንዴት ምርጫው ሊካሄድ ይችላል የሚል ጥያቄ ይነሳልና በዚህ ላይ ምን ምላሽ አለዎት?
አቶ ዛዲግ፡- ለምርጫ ሲባል ሰው ማሰር ከቆመ 3 ዓመት ሆኖታል፡፡ ምርጫ ለማሸነፍ ማሰር አይጠበቅብንም፤ አይገባምም፡፡ ሃሳብ አለን ግዙፍ መዋቅር አለን እነዚህ ምርጫ ለማሸነፍ በቂ ናቸው ብለን እናስባለን፡፡ ከተሸነፍን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡ ምርጫ ለማሸነፍ ስንል የምናስረው አንድም ፖለቲከኛ የለም፡፡
ግን ደግሞ ፖለቲከኞች ሰዎች ዜጋ ናቸውና ህግ ሲጥሱ ኃላፊነት ተጠያቂነት አለ፡፡ ስለዚህ ለምርጫ ሲባል ደግሞ የህግ የበላይነትንና ተጠያቂነትን አሽቀንጥረን አንጥልም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የምርጫ ታዛቢዎችን ትፈራላችሁ?
አቶ ዛዲግ፡- ለምን እንፈራለን? ምንም የምፈራው ነገር የለም፡፡ በጠራራ ጸሃይ እንዲደረግ የምንፈልገው ነገር ነው፡፡ ብልጽግና ውስጥ ችግር ከተፈጠረ፤ የእኛ አመራር የእኛ አባል ምርጫው ላይ እክል ከፈጠሩ አስቀድመን የምናጋልጠው እኛ ነን፤ እርምጃ የምንወስደውም እኛው ነን፡፡ ያላወቅነውን ያላየነውን ነገር የሚነገሩን ታዛቢዎች ቢመጡ ደግሞ እሰዬው ብለን ግማሽ መንገድ ድረስ ሄደን እንቀበላቸዋለን፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ማንም ቢታዘብ ችግር የለባችሁም?
አቶ ዛዲግ፡- ምንም ችግር የለብንም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ምርጫ ቦርድ በትግራይ ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ ይፋ በተደረገው የምርጫ ሰሌዳ ምርጫ አይደረግም ብሏል፡፡ ለዚህ የራሱን ምክንያቶች ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ስለ ትግራይ ምርጫ በእናንተ በኩል የታሰበ ነገር አለ? ምናልባት የሚወስነው ቦርዱ ቢሆንም ምርጫው ስለሚደረግበት ጊዜ ያላችሁት ነገር አለ?
አቶ ዛዲግ፡- ምርጫ ቦርድ እንደዚህ አይደለም ያለው፡፡ ‘አይደረግም’ አላለም፡፡ ‘ሁኔታውን እየተከታተልኩ እወስናለሁ፤ ለጊዜው ከምርጫ ሰሌዳው አውጥቼዋለሁ’ ነው ያለው፡፡ አሁን ለምሳሌ ህትመቱ ትግራይም ታትሟል፤ ስልጠናም እየተሰጠ ነው፡፡
‘የጸጥታ ሁኔታውን ተከታትዬ ምርጫውን ለማድረግ የሚያስችል ከሆነ ከሃገራዊ ምርጫው ጋር ለማድረግ ይቻላል ለምን ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷል ለትግራይም ሲባል’ ነው ያለውና ሁሉም ነገር ዝግ አይደለም፡፡
እኔም ብልጽግናን ወክዬ ተገኝቼ ስለነበር የቦርዱ ሊቀመንበር ይሄን ነው ያሉት፡፡ እንደምናየው እድል አለው አብረን ብናየው ጥሩ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ብልጽግና ትግራይ ውስጥ አባላት አሉት በተለይ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ?
አቶ ዛዲግ፡- አባላት አሉት፡፡ እኛም እንደማንኛውም ፓርቲ የምልመላ ስራ እንሰራለን፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- በምርጫው የመሸነፍ ስጋት አለባችሁ?
አቶ ዛዲግ፡- ማሸነፍንም መሸነፍንም እንደ አማራጭ አይተን ነው የምንገባው፡፡ በእኛ እምነት እናሸንፋለን፡፡ ሃሳባችንን የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ መንገድ ተቀብሎታል ይሄን በምርጫ ነው የምናረጋግጠው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ምርጫን የሚያሸንፈው ጠንካራ አደረጃጀት ያለው ነው፡፡ ጠንካራ አደረጃጀት አለን፡፡ እነዚህ ሁለቱ ለማሸነፍ ያግዙናል እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ነን፡፡ ከተሸነፍን ደግሞ አስበን ወስነን በጸጋ ለመቀበል ነው የምንገባው፡፡ ስለዚህ በእኛ እምነት ብዙ እኛን የሚገዳደር ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አለ ብለን አናምንም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የብልጽና ፓርቲ አባል ለመሆን ምንድነው መስፈርቱ?
አቶ ዛዲግ፡- ኢትዮጵያዊ መሆን፣ በህግ የበላይነት ማመን እና በመሃል ፖለቲካ ከዋልታ ረገጥነት ውጪ የሆነን ፖለቲካ መቀበል ይጠይቃል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- እናንተ ፓርቲ ውስጥ ያሉት እንደዛ አይነት ናቸው ወይ?
አቶ ዛዲግ፡- የአስተሳሰብ ግንባታ ብዙ ስራ ይጠይቃል፡፡ ብልጽግና አንድ ዓመቱ ነው ከተመሰረተ፡፡ በመርህ ደረጃ ሁሉም የመሃል ፖለቲካን ተቀብሎ ነው የገባው፡፡ እዛና እዚህ ወጣ ገባዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህም ማስተካከል አስተሳሰባቸውን መግራት፣ አቅማቸውን መገንባት፣ የመሃል ፖለቲካን ጥቅም እንዲገነዘቡ ማድረግ የፓርቲው ስራ ነው፤ እየሞከርን ነው፡፡ አልሆን ሲል ደግሞ በመሃል ፖለቲካ የማያምኑ በዋልታረገጥ ፖለቲካ ውዥንብር ውስጥ የሚገባ ካለ ደግሞ ወደሚያምንበት እንዲሄድ እናደርጋለን፡፡ በመሰረታዊነት የምናስቀድመው ግን ግንባታን ነው፡፡ የአመለካከት ቀረጻን ነው፤ ያን እየሰራን ነው፡፡ በእኛ እምነት ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ተፎካሪ ፓርቲዎች እንደልብ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት አስቻይ የፖለቲካ ሁኔታ ተፈጥሯል?
አቶ ዛዲግ፡- አዎ! ቅድም ያልኩት እኮ ነው፡፡ እንቅስቃሴ ትንሹ ነገር ነው፡፡ ከዚያ በላይ ሄደናል፡፡ እንደፈለጉት እንዲንቀሳቀሱ እንዲፈትኑን እንፈልጋለን፡፡ ተፈትነን የምናልፍበት ምርጫ እንጂ እንዳይንቀሳቀሱ ሸብበን በዛ ብልጫ አግኝተን እንድናሸንፍ የምንፈልገው ምርጫ አይደለም፡፡ ይሄ ለኢትዮጵያ ህዝብም ለእኛም ታሪካዊ ምርጫ ነው፡፡ አንድ የማይገኝ እድል ነው፡፡ ብዙ የባከኑ እድሎች አሉ፤ ይሄንኛውም ከባከኑት እድሎች አንዱ እንዲሆን አንፈልግም፡፡ ስለዚህ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ እንፈልጋለን፡፡ ይሄን የሚጥስ አካል ሲኖር ደግሞ ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የህግ ማስከበር ዘመቻው ሙሉ በሙሉ አለመጠናቀቅ በምርጫው ላይ ተጽዕኖ አይኖረውም?
አቶ ዛዲግ፡- በእኛ እምነት በከፍተኛ ፍጥነት ዋናው ምዕራፍ ተጠናቋል ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ነው የሄድነው ትልልቅ አመራሮች ተይዘዋል፤ የተቀረው በጣም ትንሽ ነገር ነው ስለዚህ እንዲያውም ይሄ ዘመቻ በአጭር ጊዜ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መጠናቀቁ የመንግስትን ዘመቻ የማስፈጸም ብቃቱን ያሳያል።
አል ዐይን አማርኛ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
አቶ ዛዲግ፡- እኔም አመሰግናለሁ