ኢሰመኮ በጋምቤላ ክልል የህጻናትና ህወሓትን “ይረዳሉ” የተባሉ እስረኞች ጉዳይ አሳሳቢ ነው አለ
ኢሰመኮ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ በነጻነት ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን አስታውቋል
ኢሰመኮ በክልሉ በቁጥጥር ስር በዋሉ 90 የትግራይ ተወላጆች ላይ ምርመራ አለመጀመሩና በዋስትና አለመለቀቃቸው አሳሳቢ ነው ብሏል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ ከታህሳስ 12 እስከ 15፣2013ዓ.ም በጋምቤላ ክልል በመሰማራት ባደረገው ዳሰሳ መሰረት የእስረኞች አያያዝና የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ ጉዳይ ችግር ውስጥ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ”ሕፃናት እስረኞችና የተጠርጣሪ ታሳሪዎችን የዋስትና መብት ማረጋገጥ እጅግ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል“ ማለታቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
ኢሰመኮ በክልሉ ህውሓትን በመርዳት የተጠረጠሩ ሰዎች በየትኛውም የመንግስት አካል ክስ ሳይቀርብባቸው በክልሉ ፖሊስ እስካሁን መታሰራቸው እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡
በኦነግ ሽኔ አባልነት ተጠርጥረው“…በጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት ከታኅሣሥ ወር መግቢያ ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሁለት የ 11 እና የ 12 ዓመት ሕፃናት ወንዶች፣ እንዲሁም አንድ የ14 ዓመት ሕፃን ሴት በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ”ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡
ህወሃትን ይረዳሉ ተብለው “በአብዛኛው የትግራይ ተወላጅ በሆኑ 90 ተጠርጣሪዎች” ላይ እስካሁን ምርመራ አለመጀመሩንና ይህንንም ለክልሉ ቢያሳውቅም እስካሁን አልተለቀቁም ብሏል፡፡ኢሰመኮ ማረሚያ ቤት ከመጎብኘት በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማነጋጋሩን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኢስመኮ እንደገለጸው በክልሉ ያሉ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዘዋውረው ለመስራትና ቢሮ ለመክፈት መቸገራቸውን ገልጸዋል ብሏል፡፡ በክልል የገዥው ፓርቲ አባል ባልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ለ”ብልጽግና ፓርቲ” አባልነት ክፈሉ እየተባሉ ጫና እንደሚደርስባቸው የገለጸ ሲሆን አሁን የእርምት ርምጃ በመወሱ በበጎ እንደሚያየው ገልጿል፡፡