የኔቶ አባል ለመሆን ጫፍ ላይ የደረሰችው ስቶኮልም ከአንካራ በቀላሉ ይሁንታ ታገኛለች ተብሎ አይጠበቅም
የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በትናንትናው እለት ሲከበር በስዊድን መዲና ስቶኮልም ተቃዋሚዎች በዓሉ ወደሚከበርበት መስጂድ አምርተዋል።
ከ200 በላይ የሚሆኑት ተቃዋሚዎች በመስጂዱ ዙሪያ ሆነውም በድምጽ ማጉያ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን፥ የበዓሉን አከባበርም ለማወክ ሞክረዋል።
አንድ ግለሰብም የቅዱስ ቁርአን ገጾችን በመቦጫጨቅ በእሳት ሲያያዝ ሌሎቹ “አቃጥለው” እያሉ የድጋፍ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር።
በስዊድን ጸረ እስልምና ይዘት ያላቸው ተቃውሞዎች ሲደረጉ ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም በአረፋ እለት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በተሰባሰቡበት መስጂድ ዙሪያ ቁርአን በማቃጠል የተገለጸው ተዋውሞ በርካቶችን አስቆጥቷል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን፥ ስዊድን በንግግር ነጻነት ስም ይህን መሰል ነውረኛ ተግባር እንዲደረግ መፍቀድ አልነበረባትም ብለዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ቃልአቀባይ ቬዳንት ፔታልም፥ ሃይማኖታዊ መጽሃፍትን ማቃጠል “እጅግ ልብ የሚሰብር እና ክብረነክ” ተግባር ነው ብለዋል ትናንት በሰጡት መግለጫ።
“እያንዳንዱ ህጋዊ ነገር ሁሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም” ሲሉም አክለዋል።
የስዊድን ፖሊስ ከዚህ በፊት ሊደረጉ ቁርአንን በማቃጠል ሊደረጉ የነበሩ የተቃውሞ ሰልፎችን ቢያግድም የሀገሪቱ ፍርድቤት የንግግር ነጻነትን ይቃረናል ብሎ ፈቃድ ሰጥቷል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስቴርሰን በሰጡት መግለጫም፥ ቁርአን የማቃጠሉን ጉዳይ “ተገቢ አይደለም ግን ህጋዊ ነው” በሚል አልፈውታል።
የስቶኮልም መስጂድ ኢማም ሞሃመድ ካሊፋ ግን ፖሊስ በኢድ አል አድሃ በዓል በመስጂዱ ዙሪያ የተቃውሞ ስልፍ እንዲደረግ መፍቀዱን አጥብቀው ተቃውመዋል።
“መስጂዱ ተቃውሞው ቢያንስ በሌላ አካባቢ እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፤ ይህንንም ማድረግ ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን ፖሊስ ይህን አልፈቀደም” ነው ያሉት።
የስዊድን ፖሊስ ቅዱስ ቁርአን ያቃጠለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሎ ክስ እንደመሰረተበት ቢገልጽም የቱርክ እና ስዊድን ግንኙነት ይበልጥ እየሻከረ ነው።
ስቶኮልም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን የመቀላቀል ሂደትም በአንካራ ይሁንታ ላይ እንደመመስረቱ መጓተቱ እንደማይቀር ተገልጿል።
በጥር ወር በስቶኮልም በሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ቁርአን መቃጠሉን ተከትሎ ቱርክ ከስዊድን ጋር በኔቶ ጉዳይ መነጋገር ማቆሟ ይታወሳል።