ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት በሳምንቱ መገባደጃ በስቶክሆልም ቁርአን መቃጠሉን ተከትሎ ነው
የቱርክ ፕሬዝዳንት በስቶክሆልም ቁርአን የተቃጠለበትን ተቃውሞ ተከትሎ የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ አንካራ እንደማትደግፍ አሳውቀዋል
በሳምንቱ መጨረሻ በስቶክሆልም በተደረጉ "ፀረ- እስልምና" ተቃውሞዎች ውጥረትን ተከትሎ ስዊድን ለኔቶ አባልነት ጥያቄ የቱርክን ድጋፍ መጠበቅ እንደሌለባት ኤርዶጋን ተናግረዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ስዊድን ለቱርክ ወይም ለሙስሊሞች አክብሮት ካላሳየች "በኔቶ ጉዳይ ላይ ከእኛ ምንም አይነት ድጋፍ አያገኙም" ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።
በስዊድን ዋና ከተማ ቱርክን በመቃወም እና ኩርዶችን በመደገፍ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ራስሙስ ፓሉዳን የተባሉ የዴንማርክ ቀኝ-አክራሪ ፖለቲከኛ በቱርክ ኤምባሲ አቅራቢያ ቁርአን አቃጥለዋል።
ኤርዶጋን ሰኞ እለት ቃጠሎው በተለይ ለሙስሊሞች "ስድብ" ነው ያሉ ሲሆን፤ ስዊድን ኩርድ ደጋፊ ሰልፎችን መፍቀዷን ተችተዋል።
ስዊድን ሰልፉን መፍቀድ የሚያስከትለውን ውጤት ማስላት ነበረባት ሲሉም አክለዋል።
ቱርክ ስዊድን ኔቶን እንድትቀላቀል ያቀረበችውን ተቃውሞ ለመቅረፍ የስዊድን የመከላከያ አዛዥ ወደ አንካራ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝትንም ሰርዛለች።
አንካራ ቀደም ሲል ስዊድን እና ፊንላንድ 130 የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን አሳልፈው እንዲሰጡ አስቀድማ በመጠየቅ የአባልነት ማመልከቻ ድጋፍ ለመስጠት እግሯን ጎትታ እንደነበር ፖለቲኮ ዘግቧል።
ስዊድን ግን ሁኔታው ግዙፍ እንዳልሆነ ተናግራለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቶቢያ ቢልስትሮም እንደተናገሩት ማመልከቻው ወደ እልባት ተቃርቧል ብለዋል።