ብሪታንያ በቅኝ ግዛት ዘመን በአፍሪካ ለመፈጸመችው በደል ይቅርታ እንድትጠይቅ ተጠየቀች
አዲሱ የብሪታንያ ንጉስ አፍሪካን ይቅርታ ሊጠይቁ እንደሚገባ አፍሪካዊያን ወጣቶች ጠይቀዋል
ንግስት ኤልሳቤጥ ለብሪታንያ በደል ይቅርታ ሳትጠይቅ አልፈዋል ተብሏል
ብሪታንያ በቅኝ ግዛት ዘመን በአፍሪካ ለመፈጸመችው በደል ይቅርታ እንድትጠይቅ አፍሪካውያን ወጣቶች ጠይቀዋል።
ብሪታንያን ላለፉት 70 ዓመታት በንግስትነት ያገለገሉት ንግስት ኤልሳቤጥ ዳግማዊ በተወለዱ 96 ዓመታቸው በህመም ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በነገው ዕለትም ስርዓተ ቀብራቸው እንደሚፈጸም ይጠበቃል።
የንግስቲቱን ሞት ተከትሎም የንግስቲቱ የበኩር ልጁ የሆኑት የ73 ዓመቱ ልጃቸው ልዑል ቻርልስ የብሪታንያ ንጉስ ሆነው ተሹመዋል።
ቢቢሲ በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ያሉ ወጣቶችን ስለ ንግስቲቱ ሞት ቃለ መጠይቅ ያደረገ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ እና ናይጀሪያ ደግሞ ቃለመጠይቁን ያደረገባቸው ሀገራት ናቸው።
ወጣቶቹ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ንግስት ኤልሳቤጥ ብሪታንያ በአፍሪካ እና ሌሎች አህጉራትያሉ ሀገራን ቅኝ ስትገዛ እና የተለያዩ በደሎችን ስታደርግ እውቅና ነበራቸው ብለዋል።
ይሁንና ሀገራቸው ላደረሰችው በደል አንድም ቀን ይቅርታ ሳይጠይቁ ንግስቲቱ ህይወታቸው እንዳለፈ ወጣቶቹ አክለዋል።
በተለይም የአፍሪካ ቅርሶች፣ ጌጣጌጦች እና ማዕድናት በብሪታንያ ተዘርፈው በለንደን እና ሌሎች ሙዚየሞች ውስጥ ሲቀመጡ ንግስቲቱ አንድም ቀን ቅርሶቹን ለባለቤቶቹ ይመለሱ ብለው እንደማያውቁ ወጣቶቹ ተናግረዋል።
በተለይም ብሪታንያ አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ እንቅስቃሴ ያደረጉ አፍሪካዊያን ላይ ያደረሰችው በደል መቼም ሊረሳ እንደማይችል ገልጸዋል።
ብሪታንያ በኬንያ ነጻነታቸውን ለማስከበር ማው ማው አማጺያን በሚል የተደራጁ ኬንያዊያንን ለማጥፋት በወሰደችው ዘመቻ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎች ተገድለዋል ተብሏል።
ብሪታንያ በነዚህ ኬንያዊያን ላይ ያደረሰችውን በደል ያመነች ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2013 ላይ ለአምስት ሺህ ኬንያዊያን 22 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማምታም ነበር።
እነዚህ አፍሪካዊያን ብሪታንያ በቅኝ ግዛት ዘመን ላደረሰቻቸው በደሎች ይቅርታ ልትጠይቅ እና ካሳ ልትከፍል እንደሚገባ ገልጸው አዲሱ የብሪታንያ ንጉድ ቻርልስ ይቅርታ እንዲጠይቁ እንደሚገባ ተናግረዋል።