የንግስት ኤልሳቤጥ ምስል የታተመባቸው የገንዘብ ኖቶች እና ሳንቲሞችም በሌላ ይተካሉ
የብሪታኒያ ንግስት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ በትናትናው እለት በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ላለፉት 70 ዓመታት የብሪታንያ ንግስት የነበሩት ንግስት ኤልሳቤጥ ማረፋቸውን የቤኪንግሀም ቤተ መንግሥት ይፋ አድርጓል።
የንግስት ኤልሳቤትን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ የንግስቲቱ የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ልዑል ቻርልስ የብሪታንያ ንጉስ በመሆን ተሰይመዋል።
በንጉሳውያን የዘር ሀረግ ተዋረድ መሰረት ልዑል ዊሊያም ደገሞ የአልጋ ወራሽነት ስፍራውን አሁን ንጉስ ከሆኑት ቻርልስ የሚረከቡ ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪም ንግስት ኤልሳቤጥ በዙፋን ላይ በነበሩበት ወቅት ስራ ላይ የነበሩ በርካታ ነገሮች እንደሚቀየሩ ይጠበቃል።
ከሚቀየሩት ውስጥ ቀዳሚው የብሪታኒያ ብሄራዊ መዝሙር ሲሆን፣ በዚህም ለውጥ ከሚደረግበት ውስት ፈጣሪ ንግስቲቱን ጠብቅ የሚለው ስንኝ ንጉሱን ጠብቅ ወደሚለው የሚቀየር ይሆናል።
ሌላው ለውጥ የሚደረግበት የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ሲሆን፣ በዚህም በሀገሪቱ መገበያያ በሆነው ፓውንድ ስተርሊንግ ላይ ያሉ የንግስት ኤልሳቤጥ ምስሎች በአዲሱ ንጉስ ቻርለስ ምስሎች ይተካሉ።
የፖሊስ ደንብ ልብስ ላይም ለውጥ ይደረጋል ይተባለ ሲሆን፣ ሀገሪቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ ፓስፖርት ያሉ ሰዶች ላይ ያሉ ማህተሞች እንዲሁም የፖስታ ቴምብሮችም ይቀየራሉ ተብሏል።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሙሉበሙሉ በሚባል ደረጃ ዘገባዎቻቸው በንግስቲቱ ዙሪያ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በርካታ የንግድ ድርጅቶችም ለክብራቸው ሲሉ ለተወሰነ ጊዜ ዝግ የሙደረጉ ይሆናል።
ለ70 ዓመታት የብሪታኒያ ንግስት ኤልሳቤጥ በትናንትናው እለት በ96 ዓመታቸው ማረፋቸው ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎ በመላው ብሪታንያ ሀዘን ላይ የወደቁ ሲሆን የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላም ዝቅ ብሎ ከመውለብለቡ ባለፈ የብሪታንያ ብዙሀን መገናኛዎች ሌሎች ጉዳዮችን መዘገብ አቁመዋል።
የንግስቲቱ የቀብር ስነ ስርዓት ከ10 ቀን በኋላ ክብራቸውን በጠበቀ መንገድ እንደሚከናወንም ተገልጿል።