ሙስሊሙ ማህበረሰብ “በጎ ተግባራትን በማከናወን ከፈጣሪ ዋጋ ሊያገኝ ይገባል” ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ
የ1442ኛው የረመዳን ፆም በነገው እለት እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የጨረቃ ክትትል ኮሚቴ በትናንትናው እለት ጨረቃ አለመታየቷን አስታውቆ፤ በዚህም መሠረት ዛሬ የሻዕባን ወር መጨረሻ እና 30ኛ ቀን በመሆኑ፣ የረመዳን የመጀመሪያ ቀን ማክሰኞ እንደሚሆን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ህዝበ ሙስሊሙ በፆምና ጸሎት የሚያሳልፈው የረመዳን የ1442ኛው የረመዳን ወር በነገው እለት እንደሚጀመር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ ፆሙን በማስመልከት ባስተላለፍተ መልአክት፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በታላቁ የረመዳን ፆም ወቅት “በጎ ተግባራትን በማከናወን ከፈጣሪ ዋጋ ሊያገኝ” እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመልዕክታቸው “ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጾሙን ወቅት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመንከባከብ ሊያሳልፍ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታትና ለመከላከል ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።