የኮሮና ቫይረስ በረመዳን ወቅት በሙስሊሞች ዘንድ በሚዘወተረው ቴምር አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳደረ
የኮሮና ቫይረስ በረመዳን ወቅት በሙስሊሞች ዘንድ በሚዘወተረው ቴምር አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳደረ
ቴምር በረመዳን ወቅት በሙስሊሞች ዘንድ የሚዘወተር ጣፍጭ የፍራፍሬ አይነት ነው፡፡
ሙስሊሞች ቀኑን ሙሉ ሲጾሙ ከዋሉ በኋላ ማታ ጾም ሲፈታ ሌሎች ምግቦችን ከመብላታቸው በፊት የሚቀምሱትና በረመዳን ወቅት ተፈላጊነቱ ከፍ የሚል ፍራፍሬ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከወትሮው በተለየ መልኩ ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቴምር የሚሸጡ ነጋዴዎች የአቅርቦት ችግር መኖሩን ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ተዘዋውረን በጠየቅንባቸው የመሸጫ ሱቆች የአቅርቦት ችግር መኖሩንና ከአቅርቦት ችግር የመነጨ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን ነግረውናል፡፡
ከባለፈው ዓመት አንጻር በዚህ ዓመት መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ነጋዴዎቹ ተናግረዋል፡፡ አቅርቦቱም ቢሆን ከአምናው አንፃር ቀንሷል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የታሸገ ቴምር እንደየአይነቱ በኪሎ ከ 85 ብር ጀምሮ እስከ 120 ብር ሲሸጥ፣ እየተመዘነ የሚሸጠው ቴምር ደግሞ 100፣110 እና 120 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመርካቶ በቴምር ገበያ ያገኘናቸው ዮሱፍ አሊ ሽፋው የተባሉ አባት እንደነገሩን አምና አንድ ኪሎ 100 ብር እንደገዙና ዘንድሮ ግን የለም [አቅርቦት] የለም ብለዋል:: “ነገርግን ይህም ሆኖ ደስተኛ ነኝ ፤ ችግር የለም፡፡ መስጅድ ከተፈቀደ፤ ሰላም ከሆነ መስጅዳችን ካልሆነ ደግሞ በቤታችን ረመዳንን እናሳልፈዋልን፤ ቀልድ የለም”፡፡
ኢትዮጵያ በብዛት ቴምር የምታስገባው ከሳውዲ አረቢያ፣ኦማንና እንዲሁም ሌሎች የውጭ ሀገራት በመሆኑ እና ይሄም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መመገታቱ እጥረት አጋጥሟል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ፕሬዘዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር ኢድሪስ ህዝብ ሙስሊሙ በዚህ ሳምንት የሚጀመረውን የረመዳን ጾም በተለያዩ የአምልኮ ተግባራት በማከናውን በቤቱ እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መስጅዶች ስለሚዘጉ ህዝበ ሙስሊሙ በቤቱ እንዲያከብረው ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር ኢድሪስ መምከራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡