2 የዓለም ክብረወሰኖች የሰበረው የአረብ ኢምሬትሷ ራስ አል ካይማህ ደማቅ የአዲስ አመት አቀባበል
የኢምሬትሷ ራስ አል ካይማህ ለተከታታይ 6ኛ ዓመት ክብረወሰን የሰበረ የድሮንና ርችት ትርዒት አቅርባለች
የአል ካይማህን ሰማይ ያደመቀው ትዕይንትን በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች ጎብኝተዋል
የአረብ ኢምሬትሷ ራስ አል ካይማህ ከተማ የአዲስ አመት መግባት በጉጉት ከሚጠበቅባቸው ከተሞች አንዷ ናት።
ከተማዋ በደማቅ መብራቶች አሸብርቃ ሰማይ ላይ አስደናቂ ቅርጽ እና ህብር ያላቸው ርችቶችን እየተኮሰች አዲሱን አመት ትቀበላለች።
ከተማዋ “ታሪካችን በሰማይ ላይ” በሚል መሪ ቃል የዘንድሮውን አዲስ አመት 2025 ስትቀበልም ይሄው ድምቀቷ ይበልጥ ጎልቶ በሁለት አዳስ የዓለም ክብረ ወሰኖች ታጅቦ ነው ተብሏል።
በርችት ወይም ፋየርወርክ ትዕይንት በርካታ የአለም ክብረወሰኖችን የያዘችው ራስ አል ካይማህ፥ በትናንት ምሽቱ የአዲስ ዓመት አቀባል ላይም ሁለት ክብረወሰን ያሻሻለ ትዕይንት ለእይታ አቅርባለች።
ከተማዋ ክብረወሰኖቹን “በርካታ ድሮኖችን በመጠቀም በሰማይ ላይ የተሰራ ትልቅ ዛፍ” እና “የአየር ላይ በድሮኖች የተሰራ ትልቁ የባህር ሼል ምስል” በሚል ነው ያገኘችው
በርካ ድሮኖችን ተጠቅማ የከወነችው ስነስርአት በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ እና የተለያየ ቀለማት ባላቸው መብራቶች ህብራዊ እንቅስቃሴ የታጀበ ነበር።
የ12 ደቂቃዎች ርዝማኔ ያለውን ትዕይንት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሌሊት ተነስተው ተመልክተውታል፤ ከተለያዩ ሀገራት ይህንኑ ትዕይንት ለመመልከት የመጡ ጎብኝዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ።
“መልካም አዲስ አመት 2025” የሚሉና ሌሎች በአረብኛ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን የአንድነት እሴት የሚያሳዩ መልዕክቶችም ቀርበዋል።
ርችቶቹ እስከ 1 ሺህ 100 ሜትር ከፍታ ድረስ የሚተኮሱ ስለነበሩም አል ማርጃን ከተባለችው ደሴት እስከ አል ሃምራ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተመልክተውታል።
ከ5 ኪሎሜትር ውሃ ክፍል ላይ ቀርቧል የተባለውን የአዲስ አመት መቀበያ በአካል መመልከት ያልቻሉትም በድረገጽ በቀጥታ መመልከታቸውን ዋም የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከዱባይ፣ አቡዳቢ፣ ሻርጃህ፣ አል አይን እና አጅማን በመቀጠል 6ኛዋ ግዙፍ የኤምሬትስ ከተማ ራስ አል ካይማህ በቱሪዝም ዘርፍ በፍጥነት መነቃቃት እያሳዩ ከሚገኙት መካከል ትጠቀሳለች።