የቱርኩ ፕሬዝደንት ኢርዶጋን በ2025 መጀመሪያ ኢትዮጵያና ሶማሊያን እንደሚጎበኙ አስታወቁ
በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት ያስማሙት የቱርኩ ፕሬዝደንት ታይፕ ኢርዶጋን በፈረንጁ አዲስ አመት መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል
በሁለቱ ሀገራት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው ኢትዮጵያ ከአንድ አመት በፊት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችው የወደብ ስምምነት ምክንያት ነበር
የቱርኩ ፕሬዝደንት ኢርዶጋን በ2025 መጀመሪያ ኢትዮጵያና ሶማሊያን አስታወቁ።
በሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤት ሀገራት መካከል የነበረውን አለመግባባት በስምምነት እንዲጠናቀቅ ያደረጉት የቱርኩ ፕሬዝደንት ታይፕ ኢርዶጋን በፈረንጁ አዲስ አመት መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን እንደሚጎበኙ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
"በአዲሱ አመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን እጎበኛለሁ" ብለዋል ኢርዶጋን።
ባለፈው ሳምንት ፕሬዝደንት ኢርዶጋን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን እና የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ መሀመድን በአንካራ በማግኘት አለመግባባታቸውን እንዲተው የአሸማጋይነት ሚና ተጫውተዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው ኢትዮጵያ ከአንድ አመት በፊት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችው የወደብ ስምምነት ምክንያት ነበር።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ዳርቻ ለንግድ እና ወታደራዊ ጦር ሰፈር የሚውል 20 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ በ50 አመታት የሊዝ ኪራይ እንድታገኝ፣ በምላሹ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ ያስችላል ተብሎ ነበር።
ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምታየው ሶማሊያ ስምሞነቱ ሉአላዊነቷን እና አለምአቀፍ ህግን የሚጥስ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ የግጭት አደጋ ስጋት የሚፈጥር ነው የሚል ተቃዎሞ አሰምታለች።
ይህን አለመግባባት ለመፍታት ቱርክ የሁለቱን ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአንካራ እየጠራች በተናጠል ብታናግርም ሳይሳካለት ቆይቷል። ነገርግን ባለፈው ሳምንት ያካሄደችው ንግግር ታሪካዊ ያለችውን ስምምነት ያስገኘ ሲሆን ከብራሰልስ፣ ከዋሽንግተን እና አፍሪካ ህብረት አድናቆት ተችሯታል።
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነት ባከበረ መልኩ ወደብ የማግኘት መብቷን የሚያረጋግጥ ስምምነት በአራት ወራት ውስጥ ለመድረስ ሁለቱ ሀገራት በአንካራ ተስማምተዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ቀሪ ስለመደረጉ ወይም ስላለመደረጉ በይፋ የተባለ ነገር የለም።