በጡረታ ተገልለው የነበሩ በርካታ የጤና ሙያተኞች ወደ ሙያቸው እየተመለሱ ነው
ኮሮና ጡረተኞች ሳይቀሩ ወደ ቀደመ ሙያቸው እንዲመለሱ እያስገደደ ነው
መላው ዓለምን እያዳረሰ ብዙዎችንም እየቀጠፈ ያለው የኮሮና ቫይረስ ጡረተኞች ሳይቀሩ ወደ ቀደመ ሙያቸው እንዲመለሱ እያስገደደ ነው፡፡
የ68 ዓመቷ ጁሊያና ሞራውስኪ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ጡረተኞች መካከል አንዷ ናቸው፡፡በአሜሪካ ኢሊኖይ ነዋሪ የሆኑት ጁሊያና ከ30 በላይ ዓመታት በነርስነት ወዳገለገሉበት ሆስፒታል ተመልሰው በሙያቸው ለማገልገል መወሰናቸውን ቃላቸውን የተቀበሉ የተለያዩ የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ከመቼውም ጊዜ በላይ በችግር ውስጥ ነን የሚሉት አዛውንቷ “የድንገተኛ ህክምና ክፍሎች ሌሎችም የህክምና ተቋማትም ጭምር በእንዲህ አይነት አስፈሪ ጫና ውስጥ ሆነው ተመልክቼ አላውቅም፤ይህ ደግሞ ’በቤተሰብ‘ የመጣ ነው ቤተሰብ ሲቸገር ደግሞ የአቅምን መራዳቱ የማይቀር ነው” ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
የጤና ባለሙያዎች በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ድባብ ውስጥ እንኳን ሆነው በተቻላቸው አቅም ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣትና ለብዙዎች የፈውስ ምንጭ ለመሆን እየታተሩ እንደሚገኙም አዛውንቷ ይናገራሉ፡፡
እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ተቋቁመው ያለ በቂ የህክምና ግብዓት በማገልገል ያሉት ባለሙያዎች ተግባር የሚደነቅ ቢሆንም “ሰማዕት” እንዳልሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሞራውስኪ በአሁኑ ሰዓት ለሺካጎ ጤና መምሪያ በስልክ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች እና ሃሳብ አስተያየቶች ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከእድሜያቸው መግፋት ጋር በተያያዘ ወረርሽኙ ቢያሳስባቸውም ያለአንዳች ፍርሃት ወደ ድንገተኛ ክፍል ገብተው ማገልገል እንደሚፈልጉም ነው ለሲ.ኤን.ኤን የገለጹት፡፡
የ60 ዓመቷ የኒውዮርክ ነዋሪ ላውራ ቤንሰንም እንደ ሞራዊስኪ ከ3 ዓመታት በፊት በጡረታ ወደ ተገለሉበት ሙያ ተመልሰው የማገልገል ሃሳብ ቁርጠኝነትም አላቸው፡፡
ነርሶች ራሳቸውን እንኳን ለመስጠት ቢሆን እንደማያቅማሙ የሚናገሩት ላውራ ባስፈለግሁበት በማንኛውም ሰዓት ተመልሶ በበጎ ፈቃድ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡
ለ29 ዓመታት በውስጥ ደዌ ሃኪምነት በግል ማገልገላቸውን ለኒው ዮርክ ታይም የተናገሩት የ62 ዓመቷ ኒቫ ሉቢን ጆንሰንም ከ3 ዓመታት በፊት ወደ ተዉት ሙያ ለመመለስ ፍላጎት እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡
“ለቫይረሱ ሊያጋልጥ በሚችል የእድሜ ክልል ውስጥ እገኛለሁ፤ተያዥ የጤና ችግሮችም አሉብኝ፤ባለቤቴም ከ70 በላይ ዓመታትን ያስቆጠረ አዛውንት ነው” ያሉት እንዲህ ዓይነት ስጋቶች ቢኖሩብኝም ሙያዊ አበርክቶ እንዲኖረኝ በኢሜይል ለጠየቀኝ አንድ የግል ተቋም ለደንበኞቹ በስልክ የማማከር አገልግሎትን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ብለዋል፤ ከ10 እና 15 ዓመታት በፊት ባልነበረው የአገልግሎት መንገድ ለማገልገል የሚያስችለውን እድል በማግኘታቸው ደስ መሰኘታቸውን እና የባለሙያዎችን ጫና ሊያቀል እንደሚችል በመጠቆም፡፡
የባለፈው ዓመት የ‘ወይዘሪት እንግሊዝ’ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የ24 ዓመቷ ብሃሻ ሙከርጂም ወደ ተመረቀችበት የህክምና ሙያ እንደምትመለስ አስታውቃለች፡፡
በህንድ የነበሯትን የበጎ አድራጎት ተግባራት አቋርጣ ወደ ሃገሯ የተመለሰችው ብሃሻ ለቀጣይ 14 ቀናት ራሷን አግልላ ከቆየች በኋላ በሙያዋ ማገልገል ትጀምራለችም ተብሏል፡፡
ቫይረሱ በኢትዮጵያ ሊደቅን የሚችለውን አስከፊ ችግር ታሳቢ በማድረግ መንግስት በጡረታ ለተገለሉ ሙያተኞች እና ለህክምና ተማሪዎች የብሄራዊ ግዳጅ ጥሪ ሊያቀርብ እንደሚችል ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡