ከጠዋቱ 12:00 በፊት እና ከምሽቱ 2:00 በኋላ አገልግሎት መስጠት ተከልክሏል
በአዲስ አበባ በታክሲ አገልግሎት ላይ ገደብ ተጣለ
ከነገ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ቀጣይ መመሪያ እስኪሰጥ ድረስ ማንኛውም ታክሲም ሆነ ሃይገር አውቶቡስ በአዲስ አበባ ከጠዋቱ 12:00 በፊት እና ከምሽቱ 2:00 በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጥ መወሰኑን የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቢሮው በሰጠው መግለጫ በከተማዋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የተሳፋሪ ቁጥርን በግማሽ መቀነስ የሚያስችል ውሳኔ መተላለፉንም ገልጿል፡፡
ማንኛውም ከተፈቀደው ሰው በላይ ጭኖና ከተፈቀደው ሰዓት ውጭ ሲሰራ የተገኘ ታክሲም ሆነ የሃይገር አውቶቡስ ብር 5,000 (አምስት ሺህ ብር) ቅጣት እንደሚጠብቀው ነው የተገለጸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የአሽከርካሪው መንጃ ፈቃድ እስከመጨረሻው እንዲታገድ የማድረግና በሌሎች የሀገሪቱ ህጎች ተጠያቂ የማድረግ ቅጣቶች ይጣላሉ ተብሏል፡፡