የዓለማችን ቱጃሮች ባለፉት 6 ወራት ብቻ በትሪሊዮን የሚቆጠር ሃብታቸውን አጥተዋል
የአማዞን ባለቤቱ ጄፍ ቤዞስ ደግሞ 63 ቢሊዮን ዶላር አጥቷል ተብሏል
ዙከርበርግ የሃብቱን እኩሌታ ማጣቱ ሲነገር ኤሎን መስክ ደግሞ 62 ቢሊዮን ዶላር ማጣቱ ተነግሯል
የዓለማችን ቱጃሮች ባለፉት 6 ወራት ብቻ በትሪሊዮን የሚቆጠር ሃብታቸውን ማጣታቸው ተነገረ፡፡
የናጠጡ በሚል የሚጠቀሱት ቱጃሮቹ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ አንድ ነጥብ አራት ትሪሊዬን ዶላር ያህል ማጣታቸውም ነው የተነገረው፡፡
በብሉምበርግ የቢሊዬነሮች ዝርዝር ቁጥር አንድ ቱጃር ተብሎ የሚጠቀሰው ኤሎን መስክ 63 ቢሊዮን ዶላር አጥቷል፡፡
ባካበተው 208 ቢሊዮን ዶላር አሁንም ቀዳሚ የዓለማችን ቱጃር ሆኖ የሚጠቀሰው መስክ የቴስላ እና የስፔስ ኤክስ ኩባንያዎች ባለቤት ነው፡፡
የአማዞን መስራቹ ጄፍ ቤዞስ በ129 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ቁጥር ሁለት የዓለማችን ቱጃር ነው፡፡ ሆኖም ባለፉት 6 ወራት 63 ቢሊዮን ዶላር አጥቷል ተብሏል፡፡
በቅርቡ ከእነዚህ ቁንጩ የዓለማችን ቢሊዬነሮች ተርታ ተሰልፎ የነበረው የሜታ (ፌስቡክ) ኩባንያ ባለቤትና መስራች ማርክ ዙከርበርግ ደግሞ የሃብቱን እኩሌታ ማጣቱ ነው የተነገረው፡፡ ዙከርበርግ በዓመቱ መጀመሪያ ከነበረበት የሃብት ደረጃ አሽቆልቁሎ በ60 ቢሊዮን ዶላር 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
እንደ ብሉምበርግ ከሆነ ፈረንሳዊው ቱጃር በርናርድ አርኖልት በ128 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ቁጥር ሶስቱ ያለማችን ቱጃር ነው፡፡ የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራቹ ቢል ጌትስ ደግሞ በ114 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ ነው፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ ጥር ላይ 96 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ እንደነበረው ሲነገር የነበረለት ባይናንስ የተሰኘ የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት የፋይናንስ ተቋም መስራችና ባለቤት ቻንግፔንግ ዣኦ ደግሞ በዚህ ዓመት ብቻ 80 ቢሊዮን ዶላር ማጣቱ ተነግሯል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ገንዘባቸውን ያጡ ሌሎች በርካታ ቱጃሮችም አሉ፡፡
ቱጃሮቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማነቃቃት በሚል ወደ ገበያው ሲለቀቅ ከነበረው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ብዙ ተጠቅመዋል፡፡ በተለይ የቴክኖሎጂ ተቋማቱ ብዙ ትርፍን ነው ያጋበሱት፡፡ አሁን ግን ይህ የማነቃቂያ ገንዘብ እየቀነሰ እና ሃገራትም ያጋጠማቸውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የወለድ ምጣኔን እያሳደጉ ነው፡፡
ክሪፕቶን በመሰሉ ዲጂታል ገንዘቦች ላይ ያጋጠመው ከፍተኛ የዋጋ ማሽቆልቆልም ሌላኛው ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡