የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ በአንድ ቀን 29 ቢሊየን ዶላር ማጣቱ ተገለፀ
የማርክ ዙከርበርግን የሃብት መጠን ወደ 85 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱ ተነግሯል
ማርክ ዙከርበርግ ሀብት ያሽቆለቆለው የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ ነው
ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ የሆነው ፌስቡክ ለመጀመሪያ ጊዜ አስደንጋጭ የሆነ የተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነስ እንዳጋጠመው ሜታ የተባለውና ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ኩባንያ በትናትናው እለት ባወጣው ሪፖርት ማስተወቁ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ባለፈው ሩብ ዓመት የነበረው 1.930 ቢሊየን እለታዊ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በዚህኛው ሩብ ዓመት ወደ 1.929 ቢሊየን መውረዱም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የቁጥሩን ማሽቆልቆል ተከትሎ የኩባንያው መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርብርግ በአንድ ቀን ብቻ 29 ቢሊየን ዶላር ማጣቱ ተነግሯል።
ለፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነስ በዋነኝነት ከተቀመጡት ውስጥ የተጠቃሚዎችን ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር እንዲሁም የተጠቃሚዎችን መረጃ አሳልፎ ከመስጠት ጋር የሚነሱበት ክሶች ዋነኛው ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ፌስቡክ ከተቀናቃኞቹ ቲክቶክ እና ዩትዩብ የገጠመው ፉክክርም ለተጠቃሚዎቹ መቀነስ በምክንያትነት ተቀምጧል።
የተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነሱ ፤ ሜታ ኩባንያ በስቶክ ገበያው ላይ 200 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የገበያ ዋጋን እንዲያጣ ከማድረጉ ባሻገር የዙከርበርግን የሃብት መጠን ወደ 85 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ እንዳለም የፎርብስ ዘገባ ያመለክታል።
ያጋጠመው ኪሳራ “ቢልየነሩ ማርክ ዙከርበርግ በህንድ ነጋዴዎች ሙኬሽ አምባኒ እና ጋኡታም አዳኒ በመበለጥ በቢሊየነሮች ዝርዝር 12ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታልም ነው ያለው ፎርብስ፡፡
የማርክ ዙከርበርግ የአንድ ቀን የሀብት ማሽቆልቆል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተስተዋለ ትልቁ ኪሳራ ነውም ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላኛው አሜሪካዊ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ የአማዞን በብሎክበስተር ገቢ ካገኙ በኋላ 20 ቢሊዮን ዶላር ወደ ኪሳቸው ለማስገባት በጉጉት እየጠበቁ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የአማዞን ብሎክበስተር (amazon blockbuster) የተለያየ ይዘት ያላቸው ፊልሞች እና አዝናኝ የቴሌቭዥን ፕሮገራሞች ስርጭትን የሚቀርቡበት አውታረ መረብ ነው።
በፋይናነስ ጉዳዮች ላይ ታማኝ መረጃዎችና ትንታኔዎች በመስጠት የሚታወቀው ሪፊኒቲቭ ኤኮን የተሰኘ ተቋም ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ፤ የአማዞን ኢ-ኮሜርስ ቸርቻሪ መስራች እና ሊቀመንበር የሆኑት ቤዞስ የኩባንያው 9.9% ያህል ባለቤት ናቸው።
እንደ ፎርብስ ዘገባ አሜሪካዊ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ የአለማችን ሶስተኛው ቱጃር ሰው ናቸው።