ዶናልድ ትራምፕ፤ ከፎርብስ ቀዳሚ 400 የአሜሪካ ቱጃሮች ዝርዝር ውጭ ሆኑ
በትራምፕ የቱጃርነት ታሪክ ከ25 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ እንደሆነም ነው የተነገረው
ይህ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ 600 ሚሊዮን ዶላር ማጣታቸውን ተከትሎ የሆነ ነው ተብሏል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፎርብስ ቀዳሚ የአሜሪካ 400 ቱጃሮች ዝርዝር ውጭ ሆኑ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከቱጃሮቹ ዝርዝር ውጭ የሆኑት የኮሮና ወረርሽኙን ተከትሎ 600 ሚሊዮን ዶላር በማጣታቸው ነው ተብሏል፡፡
ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝርዝሩን ተቀላቅለው ከነበረበት ከ1996 ወዲህ ማለትም ከባለፉት 25 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ ነው፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የ400ዎቹን ቁንጩ ቱጃሮች ዝርዝር ለመቀላቀል 400 ሚሊዮን ዶላር እንደጎደላቸውም ተነግሯል፡፡
ፎርብስ ትራምፕ በወረርሽኙ ምክንያት ያገኙት የነበረውን 600 ሚሊዮን ዶላር አጥተዋል ብሏል፡፡ ይህን ተከትሎ የአዛውንቱ ቱጃር አጠቃላይ የሃብት መጠን 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መሆኑንም ነው ፎርብስ ያስታወቀው፡፡
የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ፤ በሰዓታት ውስጥ 7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ ማጣቱ ተገለጸ
ባለፈው ዓመት በሃብት ደረጃቸው 339ኛው አሜሪካዊ ነበሩ፡፡ ከቀዳሚዎቹ ቁንጮ ቱጃሮች ተርታ ያሰለፋቸው 71ኛ ደረጃ ያገኙት ደግሞ በ2003 ነው፤ “ዘ አፕሬንቲስ” የሚለውን የቴሌቪዥን ፕሮግራማቸውን ከመጀመራቸው ከዓመት በፊት፡፡
በስማቸው የሚጠሩ የታዋቂ የንግድ ተቋማት ባለቤት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ በሪል እስቴት እና በአቪዬሽን ዘርፍ ከፍተኛ ስምና ዝናን አትርፈዋል፡፡
ሆኖም ከሪል እስቴት ዘርፍ በቶሎ ባለመውጣታቸው ላይ ወረርሽኙ መደረቡ ብዙ አሳጥቷቸዋል ይላል ፎርብስ፡፡
በተለይም ወረርሽኙ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከታዋቂ ዓለም አቀፍ ሆቴሎቻቸው ያገኙት የነበረውን ገቢ እንዳሳጣቸውም ነው ፎርብስ ያስታወቀው፡፡
በቅርቡ ከግዙፉ የዓለማችን የበይነ መረብ መገበያያ አማዞን ዋና ስራ አስፈጻሚነት የለቀቀው ጄፍ ቤዞስ ቁንጮ ከተባሉት 400 አሜሪካውያን ቱጃሮች ቀዳሚ ሲሆን የቴስላ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አምራቹ ኤለን መስክ ይከተለዋል፡፡