“ይህኛውንና ቀጣዩን የውድድር ዘመን እጫወታለሁ፤ ሰውነቴ ከፈቀደ መጫወቴን እቀጥላሁ” ብሏል
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከ2026 በፊት ራሱን ከእግር ኳስ እንደማያገል አስታወቀ።
ለሳዑዲ አረቢያው አል ናሰር በመጫወት ለይ የሚገኘው ሮናልዶ፣ በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት አሳውቋል።
ሮናልዶ በአል ናሰር ያለውን የቆይታ ጊዜ ማራዘም እንደሚፈልግ ለክለቡ ባለስልጣናት ማሳወቁም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የ38 ዓመቱ ኮከብ ሮናልዶ በዚህ እድሜው በእግር ኳሱ ላይ የመንገሱን ሚስጥር ሲናገርም፣ "ሚስጥሩ ከዚህ ቀደም እንዳልኩት ጠንክሮ መስራት ነው፣ ለሰውነቴ ጥሩ እንክብካቤ አደርጋለሁ፣ ይህ ረድቶኛል" ብሏል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ መቼ እግር ኳስ መጫወት ያቆማል?
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከጋዜጠኞች በ39 እና 40 ዓመትህ በሳዑዲ ሊግ ውስጥ እንደምናይህ ተድፋ እናድርግ? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ "አዎ ደረጃ በደረጃ ታዩኛላችሁ" ብሏል።
ስለ 2026 የዓለም ዋንጫ የተጠየቀው ሮናልዶ፣ ከዓለም ዋንጫዉ በፊት እግር ኳስ እንደማያቆም እና በዓለም ዋንጫው ላይ ሀገሩ ፖርቹጋልን በመወከል መሳተፍ እንደሚፈልግም አስታውቋል።
አሁን 38 ዓመቴ ነው፣ 39፣ 40 እያለ ይቀጥላል፣ ሰውነቴ በቃህ እስኪለኝ ድረስ መጫወቴን እቀጥላለሁ ሲልም ተናግሯል።
ፖርቹጋላለዊው ኮከብ ከዚህ በፊት በሰጠው አስያየትም፣ “ሰዎች ሮናልዶ አብቅቶለታል ይላሉ፤ ግን ይህ እውነት አይደለም፤ እግሬ ክርስቲያኑ አሁን በቃኝ እስኪለኝ ድረስ መጫወቴን እቀጥላለሁ” በሏል።
“አሁንም ብዙ ይቀረኛል፤ አሁንም አግርኳስን እወዳለሁ” ያለው ክርስቲያኖ ሮናዶ፤ ጎል ማስቆጠሬንም ቀጥዬበታለሁ፤ ማሸነፍንም እወዳለሁ” ሲልም ተናግሯል።
ሰዎች እኔ በእግር ኳስ ዓለም እንዳበቃልኝ ያወራለሁ፤ እኔ ደግሞ ይህ ሀሰት እንደሆነ በስራ እያረጋገጥኩላቸሁ ነው በሏል።